የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል የአዕምሮ ህሙማኑን በየቀኑ የሚጎበኝ የጤና ባለሞያዎች ቡድን አቋቁሟል
የኤካ ኮተቤ አጠቃላይ ሆስፒታል በሜቄዶኒያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል ውስጥ የሚገኙ የአዕምሮ ሕሙማን ባሉበት እንዲታከሙ ማድረጉን አስታወቀ፡፡
የሆስፒታሉ ዋና ስራ አስኪያጅ ዶ/ር ያሬድ አግደው በሜቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል የሚገኙ 800 የሚሆኑ የአዕምሮ ህሙማንን በየቀኑ የሚጎበኝና የሚከታተል የጤና ባለሞያዎች ቡድን ተቋቁሞ ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡
የጤና ባለሙያዎች ቡድኑ የአዕምሮ ስፔሻሊስት ሀኪም ፣ ሳይኮሎጂስት (የሰነ ልቦና ባለሞያ) ፣ ሳይካትሪ ነርስ እና የሳይካትሪ ማስተርስ ነርስ ያካተተ መሆኑን ነው ዋና ሥራ አስኪያጁ የገለጹት፡፡
ይህም በማዕከሉ የሚገኙ የአዕምሮ ህሙማን ወደ ጤና ተቋማት መሔድ ሳያስፈልጋቸው ባሉበት ህክምናውን እንዲያገኙ ያስችላቸዋል ተብሏል፡፡
በቀጣይ የኤካ ኮተቤ አጠቃላይ ሆስፒታል ከሜቄዶኒያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል ጋር በትብብር ለመስራት የመግባቢያ ሰነድ እንደሚፈራረም ዋና ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡