ፑንትላንድ ከሶማሊያ ጋር ግንኙነቷን ባቋረጠች ማግስት ልዑኳን ወደ ኢትዮጵያ ለምን ላከች?
ፑንትላንድ በገንዘብ ሚንስትሯ መሀመድ ፋራህ የተመራ ልዑክ ወደ አዲስ አበባ በመላክ ከኢትዮጵያ ጋር መክራለች
በሳውዲ አረቢያ በህገወጥ መንገድ የሚኖሩ ከ70 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያንን የመመለሱ ስራ በሚቀጥለው ሳምንት ይጀምራል ተብላል
የፑንትላንድ ባለስልጣናት ጉብኝት በአዲስ አበባ እና የኢትዮጵያ ምላሽ
የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ነብዩ ተድላ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።
ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው ካነሷቸው ጉዳዮች መካከልም የሶማሊያ ራስ ገዝ አስተዳድር ፑንትላንድ ባለስልጣናት በኢትዮጵያ ጉብኝት ማድረጋቸው፣ የኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ የወደብ ስምምነት ጉዳይ፣ በሳውዲ አረቢያ ህይወታቸውን በአስቸጋሪ መንገድ እየኖሩ ስላሉ ኢትዮጵያዊያን ጉዳይ፣ ባለፉት ሳምንታት የተሰሩ የዲፕሎማሲ ጉዳዮች እና ሌሎችም አጀንዳዎች ዋነኞቹ ነበሩ።
ፑንትላንድ ከሶማሊያ ፌደራል መንግሥት ጋር ያላትን ግንኙነት ባቋረጠች በማግስቱ ልዑኳን ወደ ኢትዮጵያ ለምን ላከች? የጉብኝቱስ አላምስ ምንድን ነው? በአዲስ አበባ በነበራቸው ቆይታም ምን ምን ላይ ተወያዩ? በሚል ለቃል አቀባዩ ከጋዜጠኞች ጥያቄዎች ቀርበዋል።
አቶ ነብዩም በፑንትላንድ የገንዘብ ሚንስትር መሀመድ ፋራህ የተመራ ልዑክ በኢትዮጵያ ጉብኝት ማድረጉን ተናግረው ይህ የአዲስ አበባ ጉብኝት ከሰሞኑ ወቅታዊ ጉዳይ ጋር የማይገናኝ እንደሆነ እና ፕሮግራሙም የቆየ ቀጠሮ ነው ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ሌላኛው ለቃል አቀባዩ ከጋዜጠኞች የተነሳላቸው ጥያቄ ኢትዮጵያ ከሌላኛዋ የሶማሊያ ራስ ገዝ ነኝ ከምትለው ሶማሊላንድ ጋር ያደረገችው የወደብ መግባቢያ ስምምነት ጉዳይ ምን ደረሰ? የሚል ሲሆን ቃል አቀባዩም " በቀጣይ ስለ ስምምነቱ አዲስ ነገር ሲኖር ይፋ እናደርጋለን" በሚል ተጨማሪ ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
በሳውዲ አረቢያ በእስር ላይ እና አስቸጋሪ ህይወት እየኖሩ ያሉ ከ70 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያንን ወደ ሀገራቸው የመመለስ ስራው በቀን 100 ሰዎችን መመለስ ተጀምሯል ተብሏል።
ይሁንና "በእስር ቤት ያሉ ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ተከትሎ ዜጎቻችንን ቀስ በቀስ ከመመለስ ይልቅ በዘመቻ መልክ ለመመለስ ታቅዷል" ሲሉም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።
ይህን ኢትዮጵያዊያንን በዘመቻ የመመለስ ስራውን ለማቀላጠፍ የፊታችን ቅዳሜ በአምባሳደር ብርቱካን አያኖ የተመራ ልዑክ ወደ ሪያድ እንደሚያቀናም ተገልጿል።
ከሁለትዮሽ ውይይቱ በኋላም በሳምንት 12 በረራዎችን በማድረግ ኢትዮጵያዊያን ዜጎችን ወደ ሀገራቸው መመለስ እንደሚጀመር ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።