ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሃመድ ወደ አስመራ ያቀኑት በፕሬዝዳንት ኢሳያስ ግብዣ ነው ተብሏል
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሃመድ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት በዛሬው እለት ኤርትራ ገብተዋል።
ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሃመድ ለሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት አስመራ ሲደርሱም ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሃመድ ወደ አስመራ ያቀኑት በፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ግብዣ እንደሆነም ነው የተነገረው።
ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሃመድ በኤርትራ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ስያደርጉ ይህ በሁለት ወራት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሃመድ ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ስምምነት በኋላ የመጀመሪያ የውጭ ሀገር ጉዟቸውን በኤርትራ ማድረጋቸው ይታወሳል።
ፕሬዝዳንቱ በአስመራ ቆይታቸው ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር በሁለትዮሽ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ በስፋት መወያየታቸውም ተነግሯል።
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሃመድ በወቅቱ ከኤርትሪያ ቲቪ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ “ኤርትራን በተደጋጋሚ ጎብኝቻለሁ፤ ለኛ ኤርትራ ቤታችን ናት፤ እዚህ የመጣነው ኤርትራ ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገች ባለችበት በሶማሊያ ሽብርተኝነትን መዋጋት ዙሪያ ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ ገለጻ ለማድረግ ነው ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሃመድ አከልውም “ኤርትራ የሶማሊያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ለማስጠበቅ ስትደግፍ መቆየቷን እና ይህም የኤርትራ አለም አቀፍ አቋም” መሆኑን ገልጸለዋል።