ሶማሊያና ቱርክ የተፈራረሙት ወታደራዊ ስምምነት በኢትዮጵያ ላይ ተጽዕኖ ይኖረዋል?
የሶማሊያ ፓርላማ ከቱርክ ጋር የተደረሰውን የ10 አመት ወታደራዊ ትብብር ስምምነት በዛሬው እለት አጽድቋል
ስምምነቱ ሶማሊያ ሉአላዊነቷንና የባህር ክልሏን ለማስጠበቅ ከቱርክ ድጋፍ እንድታገኝ ያስችላታል ተብሏል
የሶማሊያ ፓርላማ ከቱርክ ጋር የተደረሰውን የወታደራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትብብር ስምምነት በዛሬው እለት አጽድቋል።
ከ13 ቀናት በፊት የሁለቱ ሀገራት የመከላከያ ሚኒስትሮች በአንካራ የፈረሙትና በዛሬው እለት የጸደቀው ስምምነት ዝርዝር ጉዳዮች ይፋ አልተደረገም።
የሶማሊያ መገናኛ ብዙሃን ግን ለ10 አመት ይቆያል በተባለው ስምምነት ቱርክ ለሶማሊያ ባህር ሃይል ስልጠና እና የቁሳቁስ ድጋፍ እንደምታደርግ ገልጸዋል።
ሞቃዲሾ በግዛቷ የባህር ክልል ውስጥ ሽብርተኝነት፣ የባህር ላይ ውንብድና እና “የውጭ ጣልቃገብነትን” ለመከላከልም አንካራ ድጋፍ ታደርጋለች መባሉን አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
የሶማሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሃምዛ አብዲ ባሬ ከቱርክ ጋር የተደረሰው የወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ ትብብር ስምምነት “ሶማሊያ በአለማቀፍ መድረክ ሀቀኛ አጋር” እንዳላት ማሳያ መሆኑን በመጥቀስ “ዛሬ ለሶማሊያ ታሪካዊ ቀን” ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ በበኩላቸው ስምምነቱ በቀጠናው ለሚገኙ ሀገራት ስጋት የሚፈጥር እንዳልሆነ በሰጡት መግለጫ ጠቁመዋል።
ሽብርተኝነት፣ የውጭ ሃይሎች ስጋቶችን እና የባህር ላይ ውንብድናን በጋራ ለመከላከል የተደረሰው ስምምነት ከኢትዮጵያም ሆነ ከሌሎች ሀገራት ጋር ግንኙነትን የሚያሻክርና ጸብ የሚያጭር እንዳልሆነም ነው ያነሱት።
“የቱርክ ወንድሞቻችን በስምምነቱ መሰረት ባህሮቻችን ለ10 አመታት ይጠብቃሉ፤ ከ10 አመት ትብብራችን በኋላ ጠንካራ ባህር ሃይል ይኖረናል” ሲሉም ተደምጠዋል።
ኢትዮጵያ በጥር ወር መጀመሪያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችው የወደብ ኪራይ የመግባቢያ ሰነድ ሶማሊያን ማስቆጣቱ ይታወሳል።
ሶማሌላንድ የሉአላዊ ግዛቴ አካል ናት የምትለው ሞቃዲሾ የወደብ ስምምነቱ ሉአላዊነቴን የጣሰ ነው በሚል ተቃውሞዋን ስታሰማ አጋሮቿን በማስተባበርም ጫና ለማድረግ ስትሞክር ቆይታለች።
ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀመድ ባለፈው ቅዳሜ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ወታደራዊ ባለስልጣናቷን ወደ ሶማሊላንድ በመላክ የሶማሊያን “ግዛት የመውረር ዝግጅት” እያደረገች ነው የሚል ክስ ማቅረባቸው ይታወሳል።
ኢትዮጵያ ለዚህ ክስ ምላሽ ባትሰጥም በቅርቡ ለህዝብ እንደራሴዎች ምክርቤት አባላት ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር የመዋጋት ፍላጎት እንደሌላት መናገራቸው አይዘነጋም።