ፑቲን የዩክሬን ጦር ወደ ሩሲያ ዘልቆ በመግባት ውጊያ መክፈቱ “ከባድ ጸብ አጫሪ ድርጊት ነው” አሉ
በደቡብ ምዕራብ ሩሲያ ኩርስክ ክልል ከማክሰኞ ጀምሮ እያካሄዱት ባለው ውጊያ የበርካታ ሰዎች ህይወት ተቀጥፏል
የዩክሬን እና ሩሲያ ሃይሎች ከሞስኮ በ500 ኪሎሜትር ርቆ በሚገኝ አካባቢ ነው እየተዋጉ የሚገኙት
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የዩክሬን ጦር ወደ ደቡብ ምዕራብ ሩሲያ ዘልቆ መግባቱ “ከባድ ጸብ አጫሪ ድርጊት ነው” ሲሉ ተቃወሙ።
ፕሬዝዳንቱ ከሀገሪቱ ከፍተኛ የመከላከያ እና ጸጥታ ሃይል አመራሮች ጋር ባደረጉት ስብሰባ በኩርስክ ክልል ውጊያ የከፈተው የዩክሬን ጦር በፍጥነት እንዲደመሰስ አዘዋል።
የሩሲያ ጦር ከ100 በላይ የዩክሬን ወታደሮችን መግደሉንና ከ200 በላይ ማቁሰሉን ገልጿል።
የዩክሬን ወታደሮች ደግሞ አምስት ንጹሃንን መግደላቸውና ከ31 በላይ ሰዎችን ማቁሰላቸው ነው የተነገረው።
ከኩርስክ ክልል ጋር 245 ኪሎሜትሮችን የምትጋራው ዩክሬን ጦሯን ወደ ሩሲያ ያስገባችው ባለፈው ማክሰኞ ነው።
ከ1 ሺህ በላይ የዩክሬን ወታደሮች ወደ ኩርስክ የገቡት 11 ታንኮችና ከ20 በላይ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችን ይዘው ነው።
ይሁን እንጂ ድንበር ዘልቆ የገባው የዩክሬን ጦር ከባድ ኪሳራ እንደደረሰበት ነው የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ያስታወቀው።
ውጊያ እየተካሄደባት የምትገኘው ክልል አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጀች ሲሆን፥ ለተጎዱ ሰዎች በፍጥነት ለመድረስም ነዋሪዎች ደም እንዲለግሱ አሳስባለች።
ኬቭ ወደ ሩሲያ ዘልቃ ጥቃት የፈጸመችው በዶኔስክ ግዛት እየደረሰባት ያለውን ጉዳት ለመቀነስና አቅጣጫ ለማስቀየር በማለም ሳይሆን እንደማይቀር ተገምቷል።
ይሁን እንጂ መሰል ጥቃት በየወሩ ከ35 ሺህ በላይ አዲስ ምልምሎችን ለማስገባት የተገደደችውን ዩክሬን የተዋጊ ቁጥር ይበልጥ እንደሚያመናምነው ነው የሚጠበቀው።
ዩክሬን በኩርስክ ክልል እየተካሄደ ስለሚገኘው ውጊያ እስካሁን መረጃ መስጠት አልፈለገችም።
ሩሲያ ከዚህ ቀደምም ግዛቷን ዘልቀው በመግባት ጥቃት ለመፈጸም የሞከሩ የዩክሬን ወታደሮችን ፈጣን እርምጃ በመውሰድ ከሀገሯ ማስወጣቷ የሚታወስ ነው።