ሩሲያ በኪቭ አቅራቢያ የሚገኝን የዩክሬን የኃይል መሰረተልማት ከጥቅም ውጭ አደረገች
በዛይቶሚር ግዛት የተወሰኑ ክፍሎች ያሉ 68ሺ ሰዎች እና የኪቭ ግዛቶች ኃይል እንደተቋረጠባቸው ዩክሬነርጎ ገልጿል።
ሩሲያ በዩክሬን የኃይል መሰረተልማቶች ላይ መጠነሰፊ ጥቃት በማድረስ በበርካታ ግዛቶች ኃይል እንዲቋረጥ እና ዩክሬን ኃይል ከውጭ እንድታስገባ አስገድዳታለች
ሩሲያ በኪቭ አቅራቢያ የሚገኝን የዩክሬን የኃይል መሰረተልማት ከጥቅም ውጭ አደረገች።
ሩሲያ በዩክሬን ዋና ከተማ ኪቭ እና በሩሲያ ድንበር መካከል ባሉ ሁለት ግዛቶች ውስጥ በሚገኙ የኃይል መሰረተልማቶች ላይ ባደረሰችው ጥቃት በ10ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ጨለማ ውስጥ መግባታቸውን የዩክሬን ናሽናል ፓወር ግሪድ ኦፐሬተር(ዩክሬነርጎ) አስታውቋል።
ቸርኒቪህ የተባለችው የአንደኛዋ ግዛት አስተዳዳሪ የሆኑት ለዩክሬን ብሔራዊ ቴሌቪዥን እንደተናገሩት በጥቃቱ 15 ሰዎች መቁሰላቸውን እና ጥቂት መሰረተልማቶች መውደማቸውን ተናግረዋል።
በዛይቶሚር ግዛት የተወሰኑ ክፍሎች ያሉ 68ሺ ሰዎች እና የኪቭ ግዛቶች ኃይል እንደተቋረጠባቸው ዩክሬነርጎ ገልጿል።
የዩክሬን አየር ኃይል ሩሲያ ከላከቻቸው 22 ድሮኖች ውስጥ 20ዎቹን መትቶ መጣሉን አስታውቋል። አብዛኞቹ ድሮኖች በኬርሶን ደቡባዊ አቅጣጫ እና በሰሜን ምስራቅ ሱሚ ግዛት ተመትተው የወደቁ ሲሆን ሁለቱ ደግሞ በሰሜን አቅጣጫ የተመቱ ናቸው ተብሏል።
የድንገተኛ ጉዳይ አገልግሎት ሌሊቱን በተተኮሱ ድሮኖች ስድስት የመኖሪያ ህንጻዎች መመታታቸውን እና ክፍት ቦታዎች ላይ እሳት መነሳቱን ገልጿል።
ሩሲያ ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ በዩክሬን የኃይል መሰረተልማቶች ላይ መጠነሰፊ ጥቃት በማድረስ በበርካታ ግዛቶች ኃይል እንዲቋረጥ እና ዩክሬን ኃይል ከውጭ እንድታስገባ አስገድዳታለች።
የኔቶ ወደ ቀድሞ የሶቬት ሀገራት መስፋፋት ለደህንነቷ እንደሚያሰጋት በመግለጽ ነበር ሩሲያ በፈረንጆቹ የካቲት 2022 በዩክሬን ላይ ልዩ ያለችውን ወታደራዊ ዘመቻ የከፈተችው።ጦርነቱ አሁንም ቀጥሏል።
ሩሲያን ከግዛቷ ማስወጣት እንደምትችል የምትገልጸው ዩክሬን የምዕራባውያን ወታደራዊ እርዳታ እንዳይቋረጥባት ትፈልጋለች።
ምዕራባውን ሀገራት፣ ዩክሬን በልገሳ ባገኘቻቸው የረጅም ርቀት ሚሳይሎች ሩሲያ ውስጥ ያሉ ኢላማዎችን እንድትመታ ፈቅደውላታል።ሩሲያ ይህን የምዕራባውያን ውሳኔ "በእሳት መጫወት ነው" ስትል ማስጠንቀቋ ይታወሳል።