የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ 16 ወራት አልፎታል
የሩሲያዉ ፕሬዝደንት ፑቲን ዋና አጋር የሆኑት የቀድሞ የሩሲያ ፕሬዝደንት ዲሜትሪ ሜድቬዴቭ እንደተናገሩት የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ለአስርት አመታት ሊቆይ ይችላል።
የፕሬዝደንት ፑቲን የሴኩሪቲ ካውንስል ምክትል ፕሬዝደንት የሆኑት ሜድቬዴቭ ይህን የተናገሩት በቬትናም ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ነው።
ሜድቬዴቭ ብዙ ጊዜ ኃይለ ቃል በመናገር የሚታወቁ ሲሆን ባለፈው ወር የዩክሬን ባለስልጣናትን በሽታ ሲሉ መወረፋቸው ይታወሳል።
"ግጭቱ ለረጅም ጊዜ ሊቆይ ይችላል፤ ምናልባት ለአስርት አመታት ይቆያል" ሲሉ ለሩሲያው የዜና ወኪል ሪያ ተናግረዋል።
ሜድቬዴቭ እንደተናገሩት በጦርነት መሀል ተኩስ አቁም ሊኖር ይችላል፤ነገርግን ጦርነቱ እየተደገመ ይራዘማል ብለዋል።
ሜድቬዴቭ ዩክሬንን የናዚ ሀገር እያሉ ይጠሯታል።
ባለፈው ጥር ውር ሩሲያ የምትሸነፍ ከሆነ የኑክሌር ጦርነት ይከሰታል ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።
የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ 16 ወራት ሆኖታል።
ሩሲያ በዩክሬን ላይ ልዩ ያለችውን ወታደራዊ ዘመቻ የጀመረችው የምዕራባውያን ወታደራዊ ህብረት የሆነው ኔቶ ወደ የቀድሞ ሶቬት ሀገራት እየተስፋፋ መምጣቱ ለደህንነቷ እንደሚያሰጋት በመግለጽ ነበር።