ከሰሞኑ ሞስኮ ከአውሮፕላኑ መከስከስ ጋር በተያያዘ እጇ እንዳለበት ሲቀርቡ የነበሩ ክሶችን ስታስተባብል ቆይታለች
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በሩስያ አየር ክልል ውስጥ በተመታው የመንገደኞች አውሮፕላን ዙሪያ የአዘርባጃን ፕሬዝዳንትን ይቅርታ ጠየቁ፡፡
ፑቲን የ38 ሰዎች ህይወት ለጠፋበት አደጋ ግን በይፋ ሃላፊነት አልወሰዱም።
ክሬምሊን ባወጣው መግለጫ ፕሬዝዳንት ፑቲን ለአዘርባጃኑ አቻቸው ኢልሃም አሊየቭ ስልክ በመደወል በደረሰው አደጋ ማዘናቸውንና ለተጎጂ ቤተሰቦች መጽናናትን መመኘታቸውን አመላክቷል።
ፑቲን በገና ቀን የደረሰው "አሳዛኝ ክስተት" የተፈጠረው የሩሲያ አየር መከላከያ ስርአት የዩክሬን ድሮኖችን ለመምታት ጥረት ሲያደርግ ነው ማለታቸውንም ቢቢሲ ዘግቧል።
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ አደጋው ከተከሰተ ጀምሮ ምርመራው እስኪጠናቀቅ ድረስ የሩሲያን ስም ማጠልሸት እንደማይገባ ማሳሰባቸው ይታወሳል።
ፑቲን ዛሬ ይቅርታ መጠየቃቸውም ሞስኮ ከአደጋው ጀርባ አለች በሚል ሲቀርብ የነበረውን ወቀሳ የሚያረጋግጥ ነው ተብሏል።
አውሮፕላኑ በቺቺኒያ ለማረፍ ሲሞክር በሩሲያ አየር መከላከያ ተኩስ ስለተከፈተበት ወደ ካስፒያን ባህር አቅጣጫ ለመቀየር ስለመገደዱ የተለያዩ ሚድያዎች ሲዘግቡ ቆይተዋል፡፡
የአዘርባጃኑ ኢምባሪየር 190 አውሮፕላን ከባኩ ተነስቶ ወደ ቺቺኒያ መዲና ግሮዥኒ ሲያመራ በከተማዋ የነበረው ጭጋጋማ የአየር ሁኔታ የጉዞ አቅጣጫውን እንዲቀይር አድርጎታል የሚሉ ዘገባዎችም ወጥተው ነበር፡፡
ከአደጋው የተረፉ ሰዎች ደግሞ በግሮዥኒ ሰማይ ላይ በጥቂቱ ሶስት ፍንዳታ እንደሰሙና አደጋው ከአየር ሁኔታ ጋር የተያያዘ እንዳልሆነ ተናግረዋል።
የአቪየሽን ባለሙያዎችም አውሮፕላኑ የአቅጣጫ መጠቆሚያ ስርአቱ ተጠልፎ በሩሲያ የአየር መቃወሚያ ሳይመታ እንዳልቀረ ገልጸዋል፡፡
የአዘርባጃን መንግስት እስካሁን በይፋ ሩሲያን ተጠያቂ ባያደርግም የሀገሪቱ የትራንስፖርት ሚኒስትር ራሻድ ናቢየቭ አውሮፕላኑ ለማረፍ ሲሞክር "በውጭ ሃይሎች ጣልቃገብነት" ከውስጥና ከውጭ ጉዳት ደርሶበታል ብለዋል።
አዘርባጃን በአደጋው ላይ ባደረገችው ምርመራ የመጀመሪያ ግኝቶችን የሚያውቁ አራት ምንጮች የሩሲያ አየር መከላከያዎች በስህተት በአውሮፕላኑ ላይ ሳይተኩሱ እንዳልቀረ ለሮይተርስ ተናግረዋል ።
አሜሪካ በበኩሏ በካዛኪስታን ለተከሰከሰው የአዘርባጃን አውሮፕላን ሩሲያ ተጠያቂ መሆኗን የሚያሳዩ "ምልክቶች" ማግኘቷን በትላንትናው ዕለት ገልጻለች።
የዋይትሃውስ ቃልአቀባይ ጆን ኪርቢ ዝርዝር ማብራሪያ ባይሰጡበትም 38 ሰዎች ከሞቱበት አደጋ ጀርባ ሞስኮ መኖሯን የሚጠቁም መረጃ መገኘቱን አብራርተዋል።