ሩሲያ ለአዘርባጃኑ አውሮፕላን መከስከስ ተጠያቂ መሆኗን የሚያሳዩ ምልክቶች አግኝቻለሁ- ዋይትሃውስ
የሩሲያ ሲቪል አቪየሽን ተቋም በበኩሉ በቺቺኒያ ዩክሬን ተደጋጋሚ የድሮን ጥቃቶችን እንደምትፈጽም በመጥቀስ "ሁኔታው ውስብስብ ነው" ብሏል

ኬቭ 38 ሰዎች የሞቱበት አውሮፕላን የተከሰከሰው በሞስኮ ጸረ ሚሳኤል ተመቶ ነው ማለቷ ይታወሳል
ሩሲያ ባለፈው ሳምንት በካዛኪስታን ለተከሰከሰው የአዘርባጃን አውሮፕላን ምክንያት መሆኗን የሚያሳዩ "ምልክቶች" ማግኘቷን አሜሪካ ገልጻለች።
የዋይትሃውስ ቃልአቀባይ ጆን ኪርቢ ዝርዝር ማብራሪያ ባይሰጡበትም 38 ሰዎች ከሞቱበት አደጋ ጀርባ ሞስኮ መኖሯን የሚጠቁም መረጃ መገኘቱን አብራርተዋል።
ቃል አቀባዩ አሜሪካ የአውሮፕላኑ መከስከስ መንስኤን ለማጣራት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ዝግጁ መሆኗን መናገራቸውንም ዋሽንግተን ፖስት አስነብቧል።
የአዘርባጃኑ ኢምባሪየር 190 አውሮፕላን ከባኩ ተነስቶ ወደ ሩሲያዋ ቺቺኒያ መዲና ግሮዥኒ ሲያመራ በከተማዋ የነበረው ጭጋጋማ የአየር ሁኔታ የጉዞ አቅጣጫውን እንዲቀይር አድርጎታል ሲባል ቆይቷል።
ከአደጋው የተረፉ ሰዎች ግን በግሮዥኒ ሰማይ ላይ በጥቂቱ ሶስት ፍንዳታ እንደሰሙና አደጋው ከአየር ሁኔታ ጋር የተያያዘ እንዳልሆነ ተናግረዋል።
የአዘርባጃን መንግስት እስካሁን በይፋ ሩሲያን ተጠያቂ ባያደርግም የሀገሪቱ የትራንስፖርት ሚኒስትር ራሻድ ናቢየቭ አውሮፕላኑ ለማረፍ ሲሞክር "በውጭ ሃይሎች ጣልቃገብነት" ከውስጥና ከውጭ ጉዳት ደርሶበታል ብለዋል።
"ሁሉም ከአደጋው የተረፉ ሰዎች አውሮፕላኑ በግሮዥያ ሰማይ ሲበር ሶስት ጊዜ የፍንዳታ ድምጽ መስማታቸውን ተናግረዋል" ያሉት ሚኒስትሩ፥ አውሮፕላኑ በምን አይነት መሳሪያ እንደተመታ ምርመራ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የአቪየሽን ባለሙያዎችም አውሮፕላኑ የአቅጣጫ መጠቆሚያ ስርአቱ ተጠልፎ በሩሲያ የአየር መቃወሚያ ሳይመታ እንዳልቀረ ያምናሉ።
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ግን የአደጋው መንስኤ ምርመራ ሳይጠናቀቅ ሩሲያን ተጠያቂ ለማድረግ መሞከር እንደማይገባ ማሳሰባቸው የሚታወስ ነው።
የሩሲያ የሲቪል አቪየሽን ተቁምም ዩክሬን በቺቺኒያ ክልል ተደጋጋሚ የድሮን ጥቃት እንደምትፈጽም በመጥቀስ፥ በአካባቢው ያለው ሁኔታ "እጅግ ውስብስብ ነው" ብሏል።
ካዛኪስታን ደግሞ መካሰሱን ለሌሎች ትታ ከአደጋው የተረፉ 29 ሰዎች ተገቢውን ህክምና እንዲያገኙ ከአዘርባጃን ጋር በትብብር እየሰራች መሆኑን ገልጻለች።