ፑቲን የቻይና ጦር የተሳተፈበትን “ቮስቶክ 2022” የጦር ልምምድ ላይ መገኘታቸው ተገለጸ
ሩሲያና የቻይና የጦር መርከቦች በምድር ላይ ኢላማዎችን የመምታት የተኩስ ልምምድ አካሂደዋል
በቮስቶክ 2022 የጦር ልምምድ ከ14 ሀገራት የተውጣጡ 50 ሺህ ወታደሮች ተሳታፊ ሆነዋል
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን፤ ቻይናን ጨምሮ በርካታ ሀገራት በሚሳተፉበት በግዙፉ የ“ቮስቶክ 2022” የጦር ልምምድ በሚካሄድበት ካቦራቭስክ ወታደራዊ ስፍራ መገኘተቻው የክሬምሊን ቃል አቀባይ ደሚትሪ ፔስኮቭ ገለጹ፡፡
ፕሬዝዳንት ፑቲን በልምምድ ስፍራው የተገኙት ከመከላከያ ሚኒስትሩ ሰርጌይ ሾይጉ እና ከወታደራዊው አዛዥ ቫለሪ ገራሲሞቭ ጋር መሆኑን ቃል አቀባዩ፤ አስታውቀዋል።
ፕሬዝዳንቱ ለሳምንት የዘለቀውን ልምምድ የመጨረሻ ምዕራፍ እንደሚከታተሉ መገለጻቸውም ዘ-ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
በሩሲያ አስተናጋጅነት ሲካሄድ የቆየው ግዙፉ ቮስቶክ 2022 የጦር ልምምድ ባሳለፍነው ሳምንት ሀሙስ እንደተጀመረ ሚታወስ ነው፡፡
ቮስቶክ 2022 የሚል መጠሪያ የተሰጠውና በሩቅ ምስራቅ ሩሲያ እና በጃፓን ባህር ላይ ሲካሄድ የቆው ወታደራዊ ልምምድ በነገው እለት እንደሚጠናቀቅም ነው የተገለጸው፡፡
በወታደራዊ ልምምዱ አዘጋጇ ሩሲያን ጨምሮ ቻይና፣ ቤላሩስ፣ ታጃኪስታን፣ ህንድ እና ሞንጎሊያን ጨምሮ በድምሩ 14 ሀገራት ተሳትፈዋል።
በልምምዱ ከሀገራቱ የተውጣጡ 50 ሺህ ወታደሮች የተሳተፉ ሲሆን፤ የረጅም ርቀት ቦምብ ጣይ ጄቶ እንዲሁም የጦር ካርጎ አውሮፕላኖኖች የተካተቱባቸው ከ5 ሺህ በላይ የተለያዩ አይነት የጦር መሳሪያዎች ጥቅም ላይ ውለዋል፡፡
ከጦር መሳሪያዎቹ መካከልም 140 የጦር አውሮፕላኖች እና 60 የጦር መርከቦች እንደሚገኙበትም ነው የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር መረጃ የሚያመለክተው፡፡
በዚህ የጦር ልምምድ ከሚሳተፉ ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው ቻይና ፤ የጦር ልምምዱ ከወቅቱ የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ጋር እንደማይገናኝ መግለጿ ይታወሳል።
መሰል ወታደራዊ ልምምድ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን፤ የመጀመሪው የጦር ልምምድ እንደፈረንጆቹ 2018 መካሄዱ አይዘነጋም፡፡