ሩሲያና የቻይና የጦር መርከቦች በምድር ላይ ኢላማዎችን የመምታት የተኩስ ልምምድ አካሂደዋል
የቻይና እና የሩሲያ ወታደሮች የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ማድረጋቸውን የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሁለቱ ሀገራት የጋራ ወታራዊ ልምምድ ያደረጉት በሩሲያ አስተናጋጅነት እየተካሄደ በሚገኘው የቮሶቶክ 2022 ወታደራዊ ልምምድ ላይ መሆኑም ተነግሯል።
በዚሁ ልምምድ ላይ የቻይና እና የሩሲያ ወታደሮች በጋራ ወታደራዊ የኢላማ ተኩስ ልምምድ ማድረጋቸው ተገልጿል።
በዚህም የሩሲያ የፓስፊክ የባህር ኃይል እና የቻይና ባህር ኃይል ከጦር መርከቦች ላይ በመሆን የምድር ላይ ኢላማዎችን የመምታት የተኩስ ልምምድ አካሂደዋል ነው የተባለው።
እንዲሁም የሩሲያ ቲዩ-95 ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች በልምምዱ ላይ መሳተፋቸውን የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል።
በሩሲያ አስተናጋጀንት የሚካሄደው ቮስቶክ 2022 ወታደራዊ ልምምድ በሳላፍነው ሳምንት ሀሙስ በሩሲያ ሩቅ ምስራቅ ፕሪሞስኪ ግዛት መካሄድ መጀመሩ ይታወሳል
በዚህ ወታደራዊ ልምምድ ላይ አዘጋጇ ሩሲያን ጨምሮ ቻይና፣ ቤላሩስ፣ ታጃኪስታን፣ ህንድ እና ሞንጎሊያን ጨምሮ በድምሩ 14 ሀገራት ይሳተፋሉ ተብሏል።
ከሀገራቱ የተውጣጡ 50 ሺህ ወታደሮች በልምምዱ ላይ የሚሳተፉ ሲሆን፤ ከ5000 በላይ የተለያዩ አይነት የጦር መሳሪያዎች ጥቅም ላይ ይውላሉ ተብሏል።
ከጦር መሳሪያዎቹ መካከልም 140 የጦር አውሮፕላኖች እና 60 የጦር መርከቦች እንደሚገኙበትም የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር መግለጫ ያመለክታል።
በልምምዱ ላይም የሩሲያ አየር ወለድ ወታደሮች፤ የረጅም ርቀት ቦምብ ጣይ ጄቶ እንዲሁም የጦር ካርጎ አውሮፕላኖች ከሌሎች ሀገራት የጦር መሳሪያዎች ጋር በመሆን እንደሚሳተፍም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።