ፕሬዝደንት ፑቲን ቻይና ያቀረበችውን የዩክሬን የሰላም እቅድ ለምን ተቀበሉት?
"ቻይና የዩክሬይንን ቀውስ ለመፍታት ባላት አቀራረብ ላይ አዎንታዊ እይታ አለን" ብለዋል ፑቲን።
የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰርጌ ላቭሮቭ "ትልቁ የቻይና ስልጣኔ ለውይይት ያቀረበው ምክንያታዊ እቅድ ነው"ሲሉ እቅዱን ደግፈውታል
የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚረ ፑቲን በዛሬው እለታ በታተመ ቃለ ምልልሳቸው ከዩክሬን ቀውስ ጀርባ ያለውን ጉዳይ ትረዳለች ያሏት ቻይና የዩክሬን ቀውስ በሰላም እንዲፈታ ያቀረበችውን የሰላም እቅድ እንደሚደግፉት ተናግረዋል።
በቻይና ጉብኝት ከማድረጋቸው በፊት ከቻይና የዜና አገልግሎት ሺንዋ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ሩሲያ ለንግግር ክፍት መሆኗን እና ሁለት አመት ያስቆጠረው ግጭት በሰላም እንዲፈታ እንደምትፈልግ ገልጸዋል።
ፑቲን እንደገለጹት በፕሬዝደንት ሺ አማካኝነት ባለፈው ወር ይፋ የሆነው የቻይና እቅድ ከግጭቱ ጀርባ ያሉ ጉዳዮችን ከግምት ያስገባ ነው።
"ቻይና የዩክሬይንን ቀውስ ለመፍታት ባላት አቀራረብ ላይ አዎንታዊ እይታ አለን" ብለዋል ፑቲን።
"ቤጂንግ የግጭቱን መነሻ እና የአለምአቀፋዊ የጂኦ ፖለቲካ ትርጉሙን በትክክል ተረድታዋለች።"
ከአንድ አመት በፊት ቤጂንግ በመርህ ደረጃ የዩክሬኑን ጦርነት ለመቋጨት ያስችላል ያለችውን ባለ 12 ነጥብ ምክረ ሀሳብ አቅርባ ነበር፤ ነገርግን ቤጂንግ ዝርዝር ጉዳዮችን አላስቀመጠችም ነበር።
ምክረ ሀሳቡ በወቅቱ በሩሲያ እና በዩክሬን የተወሰነ ተቀባይነት ሲያገኝ፣ አሜሪካ ግን ወረራ የፈጸመችውን ሩሲያን ማውገዝ ያልቻለችው ቻይና ራሷን እንደ "ሰላምአምጭ" ቆጥራለች የሚል ትችት አቅርባ ነበር።
የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰርጌ ላቭሮቭ "ትልቁ የቻይና ስልጣኔ ለውይይት ያቀረበው ምክንያታዊ እቅድ ነው"ሲሉ ባለፈው ወር እቅዱን ደግፈውታል።
ሩሲያ፣ በዩክሬን ያለውን ጦርነት የሩሲያን ደህንነት ስጋት ከግምት ውስጥ ከማያስገባው "ኮሌክቲቭ ዌስት" ወይም ምዕራባውያን ጋር አድርጋ ነው የምታየው።
ሩሲያ "ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ" የከፈተችው ዩክሬንን ትጥቅ ለማስፈታት እና ራሷን ከፋሽስቶች ለመከላከል መሆኑን ትገልጻለች። ምዕራባውያን እና ዩክሬን ግን የሩሲያ ድርጊት "ወረራ ነው" ሲሉ ይጠሩታል።