ፑቲን ለ3ኛ ጊዜ መሪ ሆነው ለተመረጡት ፕሬዝዳንት ዢ የእንኳን ደስ አልዎት መልእክት አስተላለፉ
ፑቲን፤ በቀጣይ የዢ የስልጣን ዘመን ሞስኮ-ቤጂንግ ግንኙነት ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተስፋ አለኝ ብለዋል
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ፑቲን እና የቻይናው አቻቸው ዢ መልካም የሚባል ግንኙነት ያላቸው መሪዎች ናቸው
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላደሚር ፑቲን ለሶስተኛ ዙር የስልጣን ዘመን መሪ ሆነው ለተመረጡት የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ የእንኳን ደስ አልዎት መልእክት አስተላለፉ፡፡
ፑቲን በቀጣይ የዢ ጂንፒንግ የስልጣን ዘመን ሞስኮ-ቤጂንግ ግንኙነት ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸው ተስፋም ገልጸዋል፡፡
"በሀገራቱ መካከል ያለውን... ስትራቴጂያዊ ትብብር ለማጠናከር ያለመ ገንቢ ውይይታችንን እና የቅርብ የጋራ ስራችንን ለመቀጠል ደስተኛ ነኝ" ማለታቸውንም ነው በክሬምሊን በኩል የወጣው መግለጫ የሚያመለክተው፡፡
የሩሲያው ፕሬዝዳንት አክለው፤ ለ ዢ "ብልጽግና እና አዲስ ስኬቶች" እንደሚመኙ ተናግረዋል::
ሞስኮ እና ቤጂንግ በተለይም ከቅርብ አመታት ወዲህ ከምዕራቡ ዓለም ጋር ባለቸው ግንኙነት የቅርብ አጋሮች ሆነው ብቅ ያሉበት አጋጣሚ ተፈጥረዋል።
በሀገራቱ መሪዎች መካከል ያለው ግንኙነትም እንዲሁ መልካም የሚባል እንደሆነ ይነገራል፡፡
መሪዎቹ በቅርቡ በኡዝቤኪስታን መዲና ሳማርካንድ ተገናኝተው በሀገራቱ መካከል ያለውን ሁለንተናዊ ትብብር ለማጎልበት እንደሚሰሩ መናገራቸው አይዘነጋም፡፡
ቭላድሚር ፑቲን እና ዢ ጂንፒንግ “ዓለምን በበላይነት ለመቆጣጠር የሚደረገው ሙከራ” አንቀበልም የሚል የጋራ አቋም ያላቸው መሪዎች መሆናቸው ይታወቃል፡፡
በሌላ በኩል ቻይና ከዩክሬን ጦርነት ጋር በተያያዘ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የመነጠል አደጋ ለተጋረጠባት ሩሲያ ያላትን ድጋፍ በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች ስታንጸባርቅ ይስተዋልል፡፡
ቻይና በዩክሬን ጦርነት ጉዳይ አብዛኛው ጊዜ የመሃል አቋም ስታራምድና በሞስኮ ላይ የሚደረገው ዘመቻ ስትቃወም ነው የምትታየው፡፡
ይህም አሜሪካን ጨምሮ በምዕራባውያን ዘንዳ ባይወደድም፤ ፑቲን የቻይናው መሪ ዢ በዩክሬን ጉዳይ የሚያንጸባርቁት “ሚዛናዊ አቋም” እንደሚያደንቁ በቅርቡ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
በተጨማሪም ሀገራቱ ለዓለም ተምሳሌት የሆነ ገደብ የለሽ ትብብር ለማድረግ ከስምምነት መድረሳቸው አይዘነጋም፡፡
እናም የአሁኑ የፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ለሶስተኛ የስልጣን ዘመን መሪ ሆኖ መመረጥ በሞስኮ-ቤጂንግ መካካል ያለውን ጥሩ የሚባል ግንኙነት ወደ ከፍተኛ ደረጃ ያደርሷል ተብሎ ይጠበቃል፡፡