“አሜሪካ ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ ራሷን እንደ ፈጣሪ መልዕከተኛ አድርጋ ነው የምታስበው” - ፑቲን
ፑቲን በቅዱስ ፒተርስበርግ ከተማ በተዘጋጀ ዓለም አቀፍ የምጣኔ ሃብት ፎረም ላይ ተገኝተው ነው ይሄን ያሉት
ፑቲን የሩሲያን ምጣኔ ሃብት “ለማድቀቅ” የተደረገው ጥረት አልተሳካም ሲሉ ተናግረዋል
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የሃገራቸውን ምጣኔ ሃብት ለማድቀቅ በመደረግ ላይ ያሉ ጥረቶች አለመሳካታቸውን ተናገሩ፡፡
ፑቲን ሩሲያን ለማንኮታኮት የተደረጉ ጥረቶች አልተሳኩም ብለዋል፡፡
የሩሲያ ኢኮኖሚ በግዴለሽነት የተጣሉ ርህራሄ አልባ ማዕቀቦችን መቋቋም እንደሚችልም ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል፡፡
ቭላድሚር ፑቲን ይሄን ያሉት በቅዱስ ፒተርስበርግ ከተማ በተዘጋጀ ዓለም አቀፍ የምጣኔ ሃብት ፎረም ላይ ነው፡፡
በፎረሙ ሩሲያን ለማዳከም በማሰብ ማዕቀቦችን የሚያዘንቡ ሃገራትን በማውገዝ ከአንድ ሰዓት የበለጠ ንግግርን ያደረጉት ፑቲን ማዕቀቦቹ ራሳቸውን የሚጥሉትን ሃገራት እንደሚጎዱ ገልጸዋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት ብቻውን 400 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ጉዳትን እንደሚያስተናግድ ነውም በማሳያነት ያነሱት፡፡
በቀዝቃዛው ጦርነት አሸናፊ ሆና ብቅ ያለችው አሜሪካ ራሷን በምድር የፈጣሪ መልዕከተኛ አድርጋ ማሰብ ጀመረች ሲሉም ነው ፑቲን የተናገሩት፡፡
በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ያጋጠመው የምግብ እና የምርት መቀነስ በሩሲያ ሳቢያ የመጣ እንዳልሆነ በመጠቆምም አሜሪካ ራሷ ገንዘብ በማተምና ምርቶችን በማጋበስ የዓለም የምግብ ዋጋ እንዲያሻቅብ አድርጋለች ሲሉም ወቅሰዋል፡፡
ሃገራቸው ምግብ እና የአፈር ማዳበሪያ ግብዓቶች ወደ አፍሪካ እና ወደ መካከለኛው ምስራቅ ለመላክ ዝግጁ መሆኗንም አስታውቀዋል፡፡
ሞስኮው አሁንም በሯን ክፍት አድርጋ አብረው መስራት ከሚፈልጉ ሃገራት፤ ከምዕራባውያን ኩባንያዎች ጋር ጭምር እንደምትሰራና አዳዲስ የማስተላለፊያ መንገዶችን በመዘርጋት የነዳጅ አቅርቦቷን እንደምታሳድግም ተናግረዋል ቭላድሚር ፑቲን፡፡
ፕሬዝዳንቱ የአውሮፓ ህብረት ፖለቲካዊ ሉዓላዊነቱን መነጠቁንም ነው በመድረኩ የተናገሩት፡፡
የአውሮፓ ህብረት ዩክሬን ያቀረበችውን የአባልነት ጥያቄ መደገፉ ይታወሳል፡፡ ሆኖም ሩሲያ ህብረቱ ዬክሬንን ደካማ ጎን እየተጠቀመበት ነው ስትል ድጋፉን አውግዛለች፡፡