ፑቲን ከዩክሬን ወደ አፍሪካ ለሚገቡ የስንዴ እና የማዳበሪያ ምርቶች ሁኔታዎችን እንደሚያመቻቹ ገለጹ
ፑቲን ሩሲያ ምንጊዜም ከአፍሪካ ጎን መሆኗን መግለጻቸው ይታወሳል
ፕሬዝዳንት ፑቲን የማዳበሪያ ምርቶች አፍሪካ መድረሳቸውን ለማረጋገጥ ያላቸውን ዝግጁነትም ገልጸዋል
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከዩክሬን ወደ አፍሪካ ለሚገቡ የስንዴ ምርቶች ሁኔታዎችን እንደሚያመቻቹ ገለጹ፡፡
ፑቲን የስንዴ ምርቶች ወደ አፍሪካ መላካቸውን ለማረጋገጥ ሃገራቸው እንደምትሰራም ገልጸዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ለጉብኝት ከጋበዟቸው ከወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር እና ከሴኔጋል ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል ጋር ከጦርነቱ ጋር በተያያዙ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሶቺ ከተማ ተወያይተዋል፡፡
በውይይቱ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማትም ነበሩ፡፡
ማኪ ሳል አፍሪካ በሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ቀጥተኛ ተሳትፎ ባይኖራትም በጦርነቱ ምክንያት ሰለባ መሆኗን በውይይቱ ገልጸዋል፡፡
በተለይም ከዩክሬንና ሩሲያ ይገቡ የነበሩ የግብርና ምርቶች እና ግብዓቶች ጉዳይ አፍሪካን ለከፋ የምግብ ዋስትና ችግር እንደዳረጋትም ነው ማኪ ሳል ያስረዱት፡፡
ሩሲያን ጨምሮ የአፍሪካ አጋር የሆኑ ሁሉም ሃገራት የጣሏቸውንና በስንዴ እና በማዳበሪያ ላይ ያነጣጠሩ ማዕቀቦቻቸውን እንዲያነሱም ጠይቀዋል፡፡
ሩሲያ የምግዜም የአፍሪካ አጋር መሆኗን የገለጹት ቭላድሚር ፑቲን በበኩላቸው ከዩክሬን ወደ አፍሪካ ለሚገቡ የስንዴ ምርቶች በወደብ ላይ ለቀሩትም ጭምር ሁኔታዎችን እንደሚያመቻቹ ገልጸዋል፡፡
ሰው ሰራሽ የአፈር ማዳበሪያ ምርቶች አፍሪካ መድረሳቸውን ለማረጋገጥ ዝግጁ ስለመሆናቸውም ነው ፑቲን የገለጹት፡፡
ከ40 በመቶ የሚልቀው የአፍሪካ የስንዴ ፍጆታ በዩክሬን እና በሩሲያ የስንዴ ምርቶች የሚሸፈን ነው፡፡
ከፈረንጆቹ 2018 እስከ 2020 ባሉት ዓመታት ወደ አፍሪካ ከገባው የስንዴ ምርት ውስጥ ዩክሬን 32 በመቶውን ሩሲያ ደግሞ 12 በመቶውን ይሸፍናሉ፡፡ ለዚህም አምስት ቢሊየን ዶላር ያህል ገንዘብ ወጥቷል፡፡
ይህ መሆኑ ግብጽን መሰል ቀዳሚ ስንዴ አስመጪ ሀገራት በጦርነቱ ምክንያት ክፉኛ እንዲጎዱ ምክንያት ሆኗል፡፡