ፑቲን ሃይፐርሶኒክ ሚሳይሎችን የጫነች መርከብ ወደ አትላንቲክ ውቅያኖስ አሰማሩ
ከድምጽ ፍጥነት ዘጠኝ እጥፍ ፍጥነት ያላቸው ሚሳይሎች እስከ 1 ሺህ ኪሎሜትር ድረስ ጥቃት ማድረስ እንደሚችሉ ተገልጿል
የፑቲን ውሳኔ የዩክሬንን ጦርነትና የሩስያ፣ አሜሪካ እና ቻይናን የሃይፐርሶኒክ ሚሳይል ፉክክር ያባብሰዋል ተብሏል
ሩሲያ ሃይፐርሶኒክ ክሩዝ ሚሳይሎችን የታጠቀች መርከብ ወደ አትላንቲክ ውቅያኖስ መላኳን ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ገለጹ።
ፕሬዝዳንቱ ከሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር ሰርጌ ሾጉ እና ከመርከቧ ካፒቴን ኢጎር ክሮክማል ጋር በቪዲዮ ምክክር አድርገዋል።
ጎርስኮቭ የተሰኘችው የሀገሪቱ መርከብ ዘመናዊ ሃይፐርሶኒክ ሚሳይሎችን ታጥቃ ወደ አትላንቲክ እና ህንድ ውቅያኖሶች እንደምታመራም ፕሬዝዳንቱ በዚሁ ወቅት ገልጸዋል።
“ዚርኮርን” የሚል መጠሪያ ያላቸው ሚሳኤሎች የሚወደደራቸው እንደሌለም ነው ያነሱት።
የመርከቧ አባላት ስኬታማ ተልዕኮን እንዲፈጽሙ መልካም ምኞታቸውን የገለጹት ፑቲን፥ የተልዕኮውን ግብ ግን አልጠቀሱም።
በዩክሬኑ ጦርነት ከምዕራባውያን ጋር እሰጥ አግባ ውስጥ የገባችው ሞስኮ፥ ዛሬ ይፋ ያደረገችው ውሳኔዋ ውጥረቱን ማባባሱ እንደማይቀር ይገመታል።
የመከላከያ ሚኒስትሩ ሰርጌ ሾጉ በበኩላቸው፥ መርከቧ በአትላንቲክ እና ህንድ ውቅያኖስ ከቀዘፈች በኋላ ወደ ሜዲትራኒያን ባህር ታመራለች ብለዋል።
“ዚርኮን” ሚሳኤሎችን የታጠቀችው መርከብ በባህርም ሆነ በምድር የጠላትን ኢላማዎች መምታት ትችላለችም ነው ያሉት።
የትኛውንም የሚሳኤል መቃወሚያ አልፈው ጥቃት ማድረስ የሚችሉት ሃይፐርሶኒክ ክሩዝ ሚሳይሎች ከድምጽ ፍጥነት ዘጠኝ እጥፍ እንደሚምዘገዘጉና 1 ሺ ኪሎሜትሮችን መጓዝ እንደሚችሉም አብራርተዋል።
የመከላከያ ሚኒስትሩም በንግግራቸው የ”ጎርሽኮቭ” መርከብ የጉዞ ተልዕኮን በግልጽ አልጠቀሱም።
ተንታኞች ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሃይፐርሶኒክ ሚሳይል ልማቷን አጠናክራ የገፋችበት ሩስያ ከምዕራባውያኑ ጋር ለገባችበት ፍጥጫ ምላሽ አድርገው ይወስዱታል።
የሃይፐርሶኒክ ሚሳይሎቹ ፍጥነት ከራዳር ውጭ እንዲሆኑ የሚያደርጋቸው መሆኑ ኢላማቸውን ሳይመቱ ተመተው እንዳይወድቁ አድርጓቸዋል ነው የሚባለው።
ከሩስያ ባሳገር የቻይናም እንቅስቃሴ ያሰጋኛል ያለችው አሜሪካም የሃይፐርሶኒክ ሚሳኤሎች መቃወሚያዎችን ለመስራትና ሚሳኤሎቹን በስፋት ለማምረት በትኩረት እየሰራች ስለመሆኑ ዘናሽናል ኢንተረስት መጽሄት በቅርቡ ያወጣው ዘገባ ያሳያል።የፑቲን ውሳኔ የዩክሬንን ጦርነትና የሩስያ፣ አሜሪካ እና ቻይናን የሃይፐርሶኒክ ሚሳይል ፉክክር ያባብሰዋል ተብሏል