ፑቲን ሩሲያዊያን የሀገራቸውን ክብር ለማስጠበቅ ለመስዋዕትነት እንዲዘጋጁ አሳሰቡ
ፕሬዝዳንቱ ባስተላለፉት የአዲስ አመት መልካም ምኞት፥ የዩክሬኑን ጦርነት የሩስያን መጻኢ የሚወስን የህልውና ጉዳይ ነው ብለውታል
“የዘመኑ ናዚዎች” ያሏቸውን ምዕራባውያንንም ዩክሬንን ሩስያን ለማጥፋት እየተጠቀሙባት ነው ሲሉ ወቅሰዋል
የፈረንጆቹ አዲስ አመት 11ኛ ወሩን የያዘው የሩስያ እና ዩክሬን ጦርነት ተባብሶ የሚቀጥልበት መሆኑን የሩሲያው ፕሬዝዳንት የአዲስ አመት መልዕክት አመላክቷል።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በቀጥታ በተላለፈ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸው ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ ሲሉ የጠቀሱት ጦርነት የሩስያ የህልውና ጉዳይ መሆኑን አብራርተዋል።
የሩሲያ ወታደሮች በዩክሬን ለእውነትና ፍትህ እየተፋለሙ መሆኑን በማንሳትም ለቀጣዩ ከባድ ሃላፊነት እንዲዘጋጁ አዘዋል።
ቀጣዮቹ ወራት የሁሉንም ሩስያውያን ድጋፍና መስዋዕትነት የሚጠይቁ መሆናቸውንም ነው ፑቲን ያነሱት።
የዘጠኝ ደቂቃ ርዝማኔ ባለው የቪዲዮ መልዕክታቸው ጦርነቱን የሚቃወሙ አካላትን በራሳቸው ላይ ሞትን ያወጁ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ያለፈውን የፈረንጆቹ አመት 2022 ጀግኖች እና ሀገራቸውን ወዳጆችን ከሰነፎች እና ከሃዲዎች ለይቶ አሳይቶናል ሲሉም ነው የተደመጡት።
ፕሬዝዳንቱ ከኬቭ በኩል የቀረበውን የሩስያ ወታደሮች ከሀገሪቱ ለቀው ወጥተው ለድርድር እንቀመጥ ጥያቄም ውድቅ አድርገውታል፤ የሩስያውያንን ህልውና እና ታሪካዊ ግዛት ለማስጠበቅ ወታደሮቹ በዚያው መቆየታቸው ግድ መሆኑን በመጥቀስ።
ፑቲን በመልዕክታቸው “የዘመኑ ናዚዎች” ያሏቸው ምዕራባውያን ሞስኮ ዘመቻዋን እንድትገፋበት እየገፋፉ መሆናቸውን አንስተዋል።
“ምዕራባውያን ስለ ሰላም የሚያወሩት ውሸት ነው፤ ለወረራ እየተዘጋጁ ነው፤ ዩክሬንንም የሚጠቀሙባት ሩሲያን ለማዳከምና ለመከፋፈል ነው” ማለታቸውንም ነው ሬውተርስ ያስነበበው።
ይህ የሀገራቱ ሴራ እንዲሳካም በፍጹም አንፈቅድም ነው ያሉት።
ዩክሬንን የሰሜን አትላንቲክ የቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል ለማድረግ የተጀመረው ጥረት ሞስኮን ወደ ኬቭ ዘልቃ እንድትገባ ማድረጉ ተደጋግሞ ይነሳል።
ኬቭ እና ምዕራባውያኑ ግን ይህን የሞስኮ ውንጀላ አይቀበሉትም፤ ፑቲን በዩክሬን ወረራ የፈጸሙት የሀገራቸውን ግዛት ለማስፋፋት ነው ሲሉም ይሞግታሉ።
በ2022 ቢሊየን ዶላሮችን የሚያወጡ የጦር መሳሪያዎችን ወደ ኬቭ የላኩት ምዕራባውያን ሀገራት በ2023ም ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ አሳውቀዋል።
ጦርነቱን ለማስቆም ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት እንደ ፈረንሳይ ያሉ ሀገራት ጭምር ወታደራዊ ድጋፎችን ለማድረግ ቃል መግባታቸው የዚህ አመት ትኩረትም ኬቭ ሆና መዝለቋም አመላካች ነው።
በየካቲት ወር መጨረሻ በተጀመረው ጦርነት ሩስያ በመጀመሪያዎቹ ሳምንታት ከያዘቻቸው ቦታዎች ከግማሽ በላዩን ለቃ መውጣቷ ይታወቃል።
የሩሲያ ወታደሮች ባለፉት ስድስት ወራትም ድልን መቀዳጀት አልቻሉም።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በአዲስ አመት መልዕክታቸው ግን “የመጨረሻው ድል የኛ ነው” ብለዋል፡፡ ለዚህም ሁሉም የሀገሪቱ ዜጋ ድጋፉን እንዲሰጥና የሀገሩን ክብር ለማስጠበቅ እንዲዋደቅ አሳስበዋል፡፡