ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በመሬት ናዳ ህይወታቸውን ላጡ ኢትዮጵያውያን ሀዘናቸውን ገለጹ
የደቡብ አፍሪካ፣ የሩዋንዳና የጂቡቲ መሪዎችም ለኢትዮጵያ የሀዘን መግለጫ ልከዋል
በደቡብ ኢትዮጵያ በጎፋ ዞን በደረሰ ድንገተኛ የመሬት ናዳ አደጋ የሟቾች ቀጥር 257 ደርሷል
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ በደረሰው የመሬት ናዳ አደጋ ሕይወታቸውን ላጡ ኢትዮጵያውያን ሀዘናቸውን ገለጹ።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ለፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እና ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ባስተላለፉት መልእክት በደቡብ ኢትዮጵያ የመሬት መንሸራተት ላስከተለው አሳዛኝ ክስተት የተሰማቸውን ሀዘን መግለጻቸውን በኢትዮጵያ የሩሲያ ኤምባሲ አስታውቋል።
ፑቲን በመልእክታቸው፤ ቤተሰቦቻቸውን ላጡ ዜጎች መጽናናትን እንዲሁም በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በፍጥነት እንዲያገግሙ መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።
በተያያዘ ዜና የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ስሪል ራማፎሳ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ በደረሰው የመሬት ናዳ አደጋ ሕይወታቸውን ላጡ ኢትዮጵያውያን ሀዘናቸውን ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንት ራማፎሳ በደቡብ አፍሪካ ህዝብ ስም ለኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት መጽናናትን ተመኝተዋል።
የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜም በትናትናው እለት በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት በቀጠፈው የመሬት መንሸራተት አደጋ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና ለመላው የኢትዮጵያ የህዝብ የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ገልጸዋል።
ሩዋንዳ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ጎን እንደመትሆንም ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ አረጋግጠዋል።
የጂቡቲው ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ማር ጊሌህም አደጋው በደረሰ ማግስት ባስተላለፉት መልእክት ለመላውአ ትዮጵያውያን መጽናናትን ተመኝተዋል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጎፋ ዞን በገዜ ጎፋ ወረዳ በኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ ባሰለፍነው ሰኞ ጠዋት በደረሰ የመሬት ናዳ አደጋ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር 257 መድረሱን የተመድ እርዳታ ማስተባበርያ ቢሮ (ኦቻ ) አስታውቋል።
በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ቁጥር እስከ 500 ሊደርስ እንደሚችል ኦቻ ዛሬ ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል።