ሩሲያ ከፈረንጆቹ 1949 ጀምሮ የዚህ ምክር ቤት አባል ነበረች
ሩሲያ ከአውሮፓ ምክር ቤት ስምምነት ራሷን አገለለች።
የሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጠናቀቁን ተከትሎ በአውሮፓ ፍትህን እና ዲሞክራሲን ለማስፈን በሚል ነበር የአውሮፓ ምክር ቤት ጉባኤ የተመሰረተው።
ሩሲያን ጨምሮ በ47 የአውሮፓ ሀገራት የተቋቋመው ይህ ስምምነት የአባል ሀገራቱ ውጪ ጉዳይ ሚንስትሮች ይሳተፉበታል።
ሩሲያ ከዩክሬን ጋር ወደ ጦርነት ማምራቷን ተከትሎ ይህ ጉባኤ ሩሲያን በጊዜያዊነት ከአባልነት አግዷትም ነበር።
ይሁንና ሩሲያ አሁን ላይ ከዚህ ምክር ቤት አባልነት ራሷን ማግለሏን አስታውቃለች።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንም ሀገራቸው ከዚህ ምክር ቤት በይፋ የምትወጣበትን ረቂቅ ህግ ላይ መፈረማቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ፕሬዝዳንቱ የፈረሙበት ይህን ረቂቅ የሀገሪቱ ህግ አውጪ አካል ወይም ዱማ እንዲያጸድቅላቸው ጠይቀዋልም ተብሏል።
የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ አንድ ዓመት ሊሞላው ጥቂት ወራት ብቻ ቀርቶታል።
ዩክሬን በበኩሏ ሩሲያ መጠነ ሰፊ ጥቃት እንደከፈተችባት ገልጻ አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት በአፋጣኝ ተጨማሪ የጦር መሳሪያ ድጋፍ እንዲያደርጉላት አሳስባለች።
ኔቶ እና የፖላንድ ጠቅላይ ሚንስትር ሩሲያ የዩክሬንን ጦርነት ካሸነፈች ሶስተኛው የዓለም ጦርነት እንደሚጀመር አሳስበው ሀገራት ኬቭን እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል።