ዩክሬን የሩሲያን ጫና ለመቋቋም ከምዕራቡ ዓለም የጦር መሳሪያ ፈጥኖ እንዲደርስ አሳሰበች
የዩክሬን ጦር ሩሲያ ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ ከ70 በላይ የሮኬት ጥቃት አድርሳለች ብሏል
ምዕራባውያን ሀገራት የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ከተቀሰቀሰ ጀምሮ የማያቋርጥ የጦር መሳሪያ እያቀረቡ ነው ተብሏል
ዩክሬን ምዕራባውያን የጦር መሳሪያ አቅርቦትን እንዲያፋጥኑ አሳስባለች።
ኪቭ ይህን ያለችው ዲኒፕሮ ከተማ ከሩሲያ በደረሰባት የሚሳይል ጥቃት በአንድ የጋራ መኖሪያ ውስጥ ቢያንስ 40 ሰዎች መገደላቸውና በዩክሬን ወታደሮች በምስራቃዊ ግንባር ላይ ጫና መፈጠሩን ተከትሎ ነው ተብሏል።
የዩክሬን ጦር ጄኔራል ስታፍ ማክሰኞ እንዳስታወቁት ሩሲያ ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ ከ70 በላይ የሮኬት ጥቃት አድርሳለች።
ሩሲያ እና ዩክሬን ለሳምንታት ከባድ ጦርነት የከፈቱባትን የሶሌዳርን የጨው ማዕድን ከተማን ጨምሮ በምስራቃዊ የዶኔትስክ ክልል በባክሙት ከተማ አቅራቢያ ከሚገኙት ከ15 በላይ ሰፈሮችን የሩስያ ጦር ደብድቧል።
ሮይተርስ የማያባራ የሩሲያ ጥይት የባክሙትን ከተማ ሙሉ በሙሉ አውድሟል ያለ ሲሆን፤ በዶኔትስክ ክልል መሀል ላይ የምትገኘውን አቪዲቪካ ከተማን በእጅጉ ጎድቷል ብሏል።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪ በሰኞ ምሽት ንግግራቸው ሩሲያ በጦርነቱ ቀዳሚውን ስፍራ ለመያዝ የምታደርገው ጥረት ምዕራባውያን የጦር መሳሪያ አቅርቦትን ውሳኔ ለማፋጠን እንደሚያስገድድ አመልክቷል።
የሩስያ ጦር ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ጦርነቱን ልዩ ተልዕኮ በሚል የጀመረ ሲሆን፤ ምዕራባውያን ሀገራትም ለዩክሬን የማያቋርጥ የጦር መሳሪያ ሲያቀርቡ ከርመዋል።
ነገርግን ዘለንስኪ እና መንግስታቸው ታንኮች እንደሚያስፈልጋቸው አጥብቀው እየገለጹ ነው።
ብሪታንያ ሰኞ እለት "14 ቻሌገር" ሁለት ታንኮችን እና ሌሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ብረት ለበስ የጦር ተሽከርካሪዎችን እና የላቀ የአየር መከላከያ ሚሳይሎችን ጨምሮ ሌሎች መሳሪያዎችን እንደምትልክ አረጋግጣለች።
ጀርመን "ሊዮፓርድ" ሁለት ታንኮችን ወደ ዩክሬን እንድትልክ ጫና ውስጥ ገብታለችም ተብሏል። ነገር ግን የሀገሪቱ መንግስት እነዚያ ታንኮች መቅረብ ያለባቸው በኪየቭ ዋና አጋሮች በተለይም በዩናይትድ ስቴትስ መካከል ስምምነት ሲኖር ነው ብሏል።