ፑቲን የነጻነት ቀኗን እያከበረች ላለችው አሜሪካ የደስታ መግለጫ አለመላካቸው እያነጋገረ ነው
የአሜሪካ - ሩሲያ ግንኙነት በተለይም የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት መከሰቱን ተከትሎ እየሻከረ መምጣቱ ይገለጻል
ጉዳዩን በማስመልከት ምላሽ የሰጡት የክሬምሊን ቃል አቀባይ “ፑቲን ያደረጉት ትክክል ነው” ብለዋል
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ፑቲን የነጻነት ቀኗን እያከበረች ላለችው አሜሪካ የደስታ መግለጫ አለመላካቸው እያነጋገረ ነው፡፡
ጉዳዩን በማስመለከት ምላሽ የሰጡት የክሬምሊን ሰዎች ግን፤ ፑቲን ያደረጉት ትክክል ነው ብለዋል፡፡
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር የአሜሪካ የነጻነት ቀን በማስመልከት ለፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የእንኳን አደረሳችሁ የደስታ መግለጫ እንደማይልኩ ተነግሯል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በ“ዋሽንግተን እና በሞስኮ መካከል ያለው አሁናዊ ግንኙነት” ነው፡፡
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት "በዚህ አመት እንኳን ደስ አለዎት ማለት ተገቢ ነው ሊባል አይችልም" ምክንያቶቹ ደግሞ የአሜሪካ ፖሊሲዎች ናቸው ብለዋል።
እምብዛም ጠንካራ ነው የማይባለው የአሜሪካ - ሩሲያ የሁለትዮሽ ግንኙነት በተለይም የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት መከሰቱን ተከትሎ እየሻከረ መምጣቱን ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ሊሂቃን ሲገልጹ ይስተዋላል፡፡
ሩሲያ በዩክሬን ላይ የጀመረችውን ወታደራዊ ዘመቻን በተመለከተ፤ አሜሪካ እና አጋሮቿ በሩሲያ ላይ ያዘነቡት የማዕቀብ ናዳ፣ ለዩክሬን የሚሰጡት ወታደራዊ ድጋፍ እንዲሁም የአሜሪካ መሪዎች በተለያዩ ጊዜያት በክሬምሊን ሰዎች ላይ የሚሰነዝሩት ትችት እና ማስጠንቀቅያ የሀገራቱ ግንኙነት ይበልጥ እንዲሻክር ከማድረግ አንጻር ትልቅ ሚና እንደነበራቸውም ይገለጻል፡፡
ባይደን ከሶስት ወራት በፊት ወደ ፖላንድ አቅንተው በዋርሶው ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት “ፑቲን በስልጣን መቆየት አይችልም” የሚል ንግግራቸው ከሬምሊን ሰዎች ክፉኛ ያስቆጣ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡
ይሁን እንጅ የተናገሩት ነገር ስህተት እንደሆነ የገባቸው ባይደን በቤተ መንግስታቸው ኋይት ሃውስ በኩል በሰጡት የእርምት መግለጫ ፤ይቅርታ ፑቲን ስልጣን ላይ አይቆይም ያልኩት ከተመለከትኩት አሳዛኝ ድርጊት አንጻር እንጂ “የስርዓት ለውጥ” ማለቴ አይደለም የሚል ማስተባበያ አዘል ማስተካከያ መስጠታቸው አይዘነጋም፡፡
ሌላው ፕሬዝዳነቱ በኋላ ላይ ያጠፉት ነገር ግን፤ የአሜሪካ ጦር መጀመሪያ ወደ ዩክሬን በመግባት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ያሉበት አጋጣሚም ሩሲያ ከአሜሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት መልሳ እንድታጤን ያደረገ አጋጣሚ ነበር፡፡