ተርኪዬ "የተሰረቀ" የዩክሬን እህል የጫነችውን የሩሲያ መርከብ በቁጥጥር ስር አዋለች
ተርኪዬ የሩሲያ ባንዲራ የያዘችውን ዚቤክ- ዞሊ የጭነት መርከብ የያዘችው ከዩክሬን በቀረበ ጥያቄ መሰረት ነው ተብሏል
4 ሺ 500 ቶን እህል የጫነችው መርከብ የተነሳችው በሩሲያ ኃይሎች ስር ከሚገኘው የዩክሬን በርዲያንስክ ወደብ ነው
ተርኪዬ ከዩክሬን ተሰርቋል ያለችውን እህል የጫነችውን የሩሲያ ጭነት መርከብ በቁጥጥር ስር ማዋሏን በአንካራ የኪቭ አምባሳደር አስታወቁ።
አምባሳደር ቫሲል ቦድናር በትናንትነው እለት በዩክሬን ብሄራዊ ቴሌቪዥን እንደተናገሩት ከተርኪዬ ጋር “ሙሉ ትብብር አለን” ሲሉ ተደምጠዋል።
"መርከቧ በአሁኑ ጊዜ በተርኪዬ የጉምሩክ ባለስልጣኖች ተይዛ ወደብ መግቢያ ላይ ቆሟለችም ብለዋል አምባሳደሩ፡፡
ተርኪዬ የሩሲያ ባንዲራ የያዘችውን ዚቤክ- ዞሊ የጭነት መርከብ የያዘችው ቀደም ሲል ከዩክሬን በቀረበ ጥያቄ መሰረት ነው፡፡
በካራሱ ወደብ አቅራቢያ ከባህር ዳርቻ አንድ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው መርከቧ፤ እስካሁን ምንም አይነት ግልጽ የእንቅስቃሴ ምልክቶች እንዳልታዩባይትም ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የ 7ሺ 146 ቶን ክብደት የምትመዝነው መርከብ እጣ ፈንታ የሚወሰነው ፤ መርማሪዎች በዛሬው እለት ተገናኝተው በሚሰጡት ውሳኔ ነው ተብሏል፡፡
የዬክሬኑ አምባሳደር ግን ፤ የተርኪዬ ባለስልጣናት እህሉን ከሩሲያ ቀምተው ሊወስዱት ይችላሉ የሚል ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
ዩክሬን፤ ሩሲያ በየካቲት ወር መገባደጃ ላይ በዬክሬን ምድር ወታደራዊ ዘመቻ ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ በያዘቻቸው ግዛቶች እህል ሰርቃለች የሚል ክስ ስታቀርብ ቆይታለች።
ክሬምሊን በበኩሏ ክሱ መሰረተ ቢስ ነው በማለት ውድቅ ስታደረግ ቆይታለች፡፡
የዩክሬን የባህር ላይ አስተዳደር መረጃን ጠቅሶ የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለስልጣን ለሮይተርስ እንደተናገሩት፤ 4 ሺ 500 ቶን እህል የጫነችውና ዚቤክ ዞሊ በመባል የምትታወቀው መርከብ የተነሳችው አሁን በሩሲያ ኃይሎች ስር ከሚገኘው የደቡብ ዩክሬን በርዲያንስክ ወደብ ነው።
ዩክሬን መርከቧ በተርኪዬ ቁጥጥር ስር ውላለች ትበል እንጅ ፤ በሳካርያ ወደብ ባለስልጣናት እና የተርኪዬ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል እስካሁን ምንም የተባለ ነገር የለም፡፡