አሜሪካ ሰሜን ኮሪያ ተጨማሪ የጦር መሳሪያ ለሩሲያ ለመስጠት ማቀዷ አሳስቦኛል አለች
ኪም ጆንግ ኡን ከሩሲያ ጋር ጠንካራ ትብብርን ለመፍጠር ቃል ገብተዋል
ዋሽንግተን ሩሲያ ተጨማሪ የጦር መሳሪያዎችን ከሰሜን ኮሪያ ለማግኘት በጥብቅ እንደምትፈልግ አዲስ መረጃ አገኝቻለሁ ብላለች
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ከሞስኮ ጋር ስልታዊ ትብብርን ለማጠናከር ቃል በገቡ ማግስት ሰሜን ኮሪያ ተጨማሪ የጦር መሳሪያዎችን ለሩሲያ ለማድረስ አቅዳለች መባሉ አሜሪካን አሳስቦታል።
ኪም የሩስያ ብሄራዊ ቀንን ምክንያት በማድረግ ለሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ባስተላለፉት መልዕክት ነው ጠንካራ ትብብርን ለመፍጠር ቃል የገቡት።
ኪም ከሞስኮ ጋር "ቅርብ ስልታዊ ትብብር" ለማድረግ ጥሪ አቅርበዋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ምንም እንኳ ፒዮንግያንግ ለሩሲያ የጦር መሳሪያ እንደሸጠች ብታስተባብልም፤ ዋሽንግተን ሮኬቶችንና ሚሳይሎችን ጨምሮ በክሬምሊን ለሚደገፈው የዋግነር ቅጥረኛ ቡድን የጦር መሳሪያ መስጠቷን አረጋግጣለች ተብለዋል።
ቃል አቀባዩ አክለውም "ሰሜን ኮሪያ ተጨማሪ ወታደራዊ መሳሪያዎችን ለሩሲያ ለማድረስ ማቀዷ አሳስቦናል" ብለዋል።
አሜሪካ በመጋቢት ወር ሩሲያ በምግብ ምርት ልውውጥ ተጨማሪ የጦር መሳሪያዎችን ከሰሜን ኮሪያ ለማግኘት በጥብቅ እንደምትፈልግ አዲስ መረጃ አገኝቻለሁ ብላለች።
ዋሽንግተን በሁለቱ ሀገራት መካከል የጦር መሳሪያ ለማሻሻጥ ሞክሯል ባለችው ስሎቫኪያዊ ላይ ማዕቀብም ጥላለች።
ሰሜን ኮሪያ ባለፈው ዓመት ከተጀመረው የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት በኋላ ሞስኮን ደግፋ ከክሬምሊን ጋር የጠበቀ ግንኙነት ለመፍጠር ብርቱ ፍላጎት አሳይታለች።