ፕሬዚዳንት ፑቲን ጎረቤት ቤላሩስ ገብተዋል
ፕሬዚዳንቱ ከመከላከያ ሚኒስትራቸው ጋር ወደ ሚኒስክ ማቅናታቸው ጋብ ያለው የዩክሬን ጦርነት ጅማሮው መቃረቡን ያሳያል እየተባለ ነው
ከሶስት አመት በኋላ በቤላሩስ ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙት ፑቲን ከፕሬዚዳንት አሌክሳንደር ሉካሸንኮ ጋር ይመክራሉ
የሩስያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ለይፋዊ ጉብኝት ቤላሩስ መግባታቸው ተገልጿል።
ፕሬዚዳንቱ ሚኒስክ የገቡት ከመከላከያ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቻቸው ጋር ነው።
ይህም ከዩክሬን የምትዋሰነው ቤላሩስ በዩክሬኑ ጦርነት ከሩስያ ጎን እንድትሰለፍ ለማግባባትና ጋብ ብሎ የሰነበተውን ውጊያ ለማስጀመር ሳይታሰብ አልቀረም አስብሏል።
ከ2019 ወዲህ በቤላሩስ ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙት ፑቲን ከፕሬዚዳንት አሌክሳንደር ሉካሸንኮ ጋር እንደሚመክሩ ሬውተርስ ዘግቧል።
የቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት አካሏ ቤላሩስ የሞስኮ ሁነኛ አጋር መሆኗን ደጋግማ አሳይታለች።
የዩክሬኑ ጦርነት ሲጀመር ለመሸምገል ካደረገችውና ካልተሳካው ሙከራ ውጭ ከኬቭ በተቃርኖ መቆሟንም የሚያነሱ አሉ።
ጦርነቱ ከመጀመሩ አስቀድሞ የሩስያና ቤላሩስ ወታደሮች ያደረጉት ልምምድም የሚታወስ ነው።
የዩክሬን ባለስልጣናትም በየካቲት ወር ጦርነቱ ሲጀመር ሞስኮ ከሚኒስክ እየተነሳች ጥቃት ፈጽማብናለች በሚል ይወቅሷታል።
የክሬምሊን ቃል አቀባዩ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ግን ቤላሩስ የሩስያ ቁጥር አንድ አጋር ብትሆንም በጦርነቱ እንድትሳተፍ በሞስኮ ጫና እየተደረገባት ነው የሚለው ውንጀላ ፍጹም የተሳሳተ ነው ብለዋል።
የዩክሬን ጥምር ጦር አዛዥ ሰርሂ ናየቭ በበኩላቸው የፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጉብኝት ዋነኛ አላማ ቤላሩስ በእግረኛ ሃይል ጭምር እንድታግዛቸው ማግባባት ነው ያምናሉ።
“ሁለቱ ሀገራት የጋራ ወታደራዊ ክንፍ አደራጅተው ወታደራዊ ልምምዳቸውን ገፍተውበታል፤ ባለፈው ሳምንትም ሶስት የሩስያ አውሮፕላኖች በሚኒስክ መታየት ጉዳዩን ግልጽ አድርጎ ያሳያል” ሲሉም ተደምጠዋል።
ከፑቲን ጋር ጥብቅ ወዳጅነት አላቸው የሚባልላቸው ፕሬዚዳንት አሌክሳንደር ሉካሸንኮ ግን ቤላሩስ በዩክሬን ጦርነት እንደማትገባ ነው ደጋግመው ያነሱት።
በምዕራባውያን ማዕቀብ ውስጥ የምትገኘው ሚኒስክ ዋነኛ የወጭ ንግድ ምርቷን (ማዳበሪያ) ለመሸጥም ሆነ በተለያዩ ዘርፎች በትብብር ለመስራት ከሩስያ የቀረበ ሀገር አላገኘችም።
የሁለቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይና መከላከያ ሚኒስትሮችም የሚፈራረሟቸው ስምምነቶች የሀገራቱን ወዳጅነት ያጠናክራሉ ተብሎ ይጠበቃል።