ሩሲያ ወታደሮቿን ለማነቃቃት በጦር ግንባሮች ላይ የሙዚቃ ኮንሰርት እንደምታዘጋጅ ገለጸች
የሙዚቃ ኮንሰርቱ የሚቀርበው የወታደሮቹን የመዋጋት ሞራል ለማነሳሳት ነው ተብሏል
የብሪታንያው የስለላ ተቋም ባወጣው መረጃ የሩሲያ ወታደሮች የውጊያ ፍላጎት ቀንሷል
ሩሲያ ወታደሮቿን ለማነቃቃት በጦር ግንባሮች ላይ የሙዚቃ ኮንሰርት እንደምታዘጋጅ ገለጸች።
የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ አስር ወራት የሞላው ሲሆን ጦርነቱ እንዲቆም ብዙዎች እየጠየቁ ናቸው።
የሩሲያ መከላከያ ሚንስትር ሰርጊ ሼጉ ከዩክሬን ጋር እየተዋጋ ያለውን የሀገራቸውን ጦር ጎብኝተዋል።
ሚንስትሩ ከጉብኝቱ በኋላ እንዳሉት በጦር ግንባር ለሚገኙት የሩሲያ ወታደሮች የሙዚቃ ኮንሰርት ይቀርባል።
በጥቂት ቀናት ውስጥም የሙዚቀኞች ባንድ ወደ ዩክሬን ድንበር እንደሚላክ ቢቢሲ የሀገሪቱን መከላከያ ሚንስቴር መግለጫን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
የብሪታንያ የደህንነት ተቋም ከሰሞኑ የሩሲያ ጦር አባላት የመዋጋት ፍላጎት ማሽቆልቆሉን ይፋ አድርጎ ነበር።
ከዚህ መረጃ መውጣት በኋላም የሩሲያ መከላከያ ሚንስትር ሰርጊ ሼጉ ከዩክሬን ጋር እየተዋጋ ያለው ጦራቸውን ጎብኝተዋል።
በውጊያ ግንባሮች ላይ ላለው የሩሲያ ጦር ይቋቋማል የተባለው የሙዚቃ ባንድ ከጦሩ ውስጥም ሊውጣጣ እንደሚችል ዘገባው ላይ ተጠቅሷል።
የሩሲያ እና ዩክሬን ጦር ባክሙት በተባለችው የዩክሬን ከተማ አቅራቢያ ከባድ ውጊያ እያደረጉ እንደሆነ ተገልጿል።
ሩሲያ የዩክሬኗን ባክሙት ከተማ ለመቆጣጠር ከባድ ውጊያ እያደረገች ነው የተባለ ሲሆን ሞስኮ ይህችን ከተማ በመቆጣጠር ወደ ሌሎች የዩክሬን ከተሞች የአየር ላይ ጥቃቶችን የማድረስ እቅድ እንዳላት በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።
ሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነቱን አቁመው ወደ ድርድር እንዲመጡ ግፊት እየተደረገባቸው ሲሆን ዩክሬን ጦርነቱ የሚቆመው በሀይል ወደ ሩሲያ የተጠቃለሉ ግዛቶች እንዲመለሱላት በቅድመ ሁኔታነት አስቀምጣለች።