ፑቲን ከሳኡዲው ልኡል አልጋወራሽ መሀመድ ቢን ሳልማን ጋር ተወያዩ
ከ2019 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ፊት ለፊት የተገናኙት ሁለቱ መሪዎች በነዳጅ ዋጋ እና በእስራኤል ሃማስ ጦርነት ዙሪያ መክረዋል
የኢራኑ ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲ ዛሬ ሞስኮ ይገባሉ
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲ ከሳኡዲው ልኡል አልጋወራሽ መሀመድ ቢን ሳልማን ጋር በሪያድ ተወያዩ።
ከ2019 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ፊት ለፊት የተገናኙት መሪዎቹ እየቀነሰ የመጣውን የነዳጅ ዋጋ ለማረጋጋት መስማማታቸውን የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ተናግረዋል።
ሩሲያን ያካታተተው የአለም ነዳጅ ላኪዎች ማህበር (ኦፔክ ፕላስ) አባል ሀገራት እለታዊ የነዳጅ ሽያጫቸውን ለመቀነስ ቃል ቢገቡም የነዳጅ ዋጋ እየቀነሰ ይገኛል።
ሪያድና ሞስኮ የኢኮኖሚያቸው የደም ስር የሆነው ነዳጅ ዋጋ እንዲጨምር ይፈልጋሉ።
ይህን እውን ለማድረግ የእለታዊ ምርታቸው በምን ያህል ይገደብ የሚለው ግን ባለፈው ወር የኦፔክ ፕላስ ስብሰባን ለቀናት ማራዘሙ የሚታወስ ነው።
የሳኡዲ የኢነርጂ ሚኒስትር ኦፔክ ፕላስ ሞስኮ ለውጭ ገበያ የምታቀርበው ነዳጅ መጠን ላይ ማረጋገጫን ይፈልጋል ሲሉ መጠየቃቸውም አይዘነጋም።
በሪያዱ ውይይት ግን የአለማቀፉ የነዳጅ ዋጋ የተረጋጋ እና ተገማች እንዲሆን ፑቲን እና መሀመድ ቢን ሳልማን መግባባት ላይ መድረሳቸውን ኢንተርፋክስ ዘግቧል።
ልኡል አልጋወራሹም ሩሲያና ሳኡዲ በመካከለኛው ምስራቅ እና በአለማቀፍ ደረጃ የጋራ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ በሚያስችሉ ጉዳዮች መወያየታቸውን ገልጸዋል ብሏል የሳኡዲ ዜና አገልግሎት።
መሪዎቹ ከነዳጅ ዋጋ ባሻገር በዩክሬን እና በጋዛ ጦርነቶች ዙሪያም ምክክር ማድረጋቸው ተጠቅሷል።
የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት እንዲቆም በተደጋጋሚ ጥሪ ያቀረቡት ፑቲን የመካከለኛው ምስራቅ አጋሮቻቸው ሳኡዲ እና አረብ ኤምሬትስ በጋዛ ተኩስ እንዲቅም ጥረታቸውን እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
የኢራኑን ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲ ዛሬ በሞስኮ ሲቀበሉም የጋዛው ጦርነት የመነጋገሪያ አጀንዳቸው ይሆናል ተብሏል።
በዩክሬኑ ጦርነት በምዕራባውያን ከፍተኛ ማዕቀብ የተጣለባት ሩሲያ ከመካከለኛው ምስራቅ፣ አፍሪካ እና እስያ ሀገራት ጋር ትብብሯን ማጠናከሯን ቀጥላለች።