ፖለቲካ
ፕሬዝዳንት ፑቲን የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነትን ሞስኮ አልጀመረችውም ሲሉ በድጋሚ አረጋገጡ
ሞስኮ ጦርነቱን ለማስቆም "ልዩ ወታደራዊ ተልዕኮ" መውሰዷን ገልጸዋል
ፕሬዝዳንት ፑቲን ግጭቱ ግዛት ማስፋፋት አይደለም ብለዋል
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሀገራቸው በዩክሬን ያለውን ጦርነት እንዳልጀመረች አቋማቸውን በድጋሚ አስታውቀዋል።
ፕሬዝዳንቱ ይልቁንም ሞስኮ ጦርነቱን ለማስቆም "ልዩ ወታደራዊ ተልዕኮ" ያለችውን እርምጃ መውሰዷን ገልጸዋል።
የዓለም ግዙፍ ሀገር የሆነችው ሩሲያ ከዩክሬን ግዛት መውሰድ አያስፈልጋትም ሲሉም የምዕራባዊያንን ትችት አጣጥለዋል።
ምዕራባዊያን በበኩላቸው ጦርነቱ የዩክሬንን ግዛት ለመቀማት በሩሲያ የተጀመረና የመስፋፋት ፍላጎት መሆኑን በተደጋጋሚ ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንት ፑቲን ግጭቱ ለግዛት ማስፋፋት ሳይሆን፤ የዓለም ስርዓትን ለማስፈን ነው ብለዋል።
ዓለምን የመቆጣጠር ስልጣናቸው ያበቃላቸው ምዕራባዊያን ሁሌም ጠላት ይፈልጋሉ ሲሉ የተቹት ፕሬዝዳንቱ፤ ከገሀዱ ዓለም አፈንግጠዋል በማለት አቋማቸውን አጣጥለዋል።
በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ምዕራባዊያን በመተባበር ኪየቭን እየደገፉ ነው።
ሆኖም ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ እርዳታው እንዲጠናከር እየወተወቱ ነው።
አፍሪካን ጨምሮ ሁለቱን ሀገራት ለማሸማገል የተደረጉ ጥቂት ጥረቶች ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላት ባለመቻላቸው ዳር መድረስ አልቻሉም።