የሩሲያ ጦር መሳሪያዎች “እንደ ኬክ” እየተሸጡ ነው ሲሉ ፕሬዝዳንት ፑቲን ተናገሩ
ፕሬዝዳንት ፑቲን የሩሲያ ጦር መሳሪያዎች ከኔቶ አቅም በላይ ናቸውም ብለዋል
ፕሬዝዳንቱ አክለውም የሩሲያ ኢኮኖሚ ከአውሮፓ ቀዳሚው ከዓለም ደግሞ አምስተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል
የሩሲያ ጦር መሳሪያዎች “እንደ ኬክ” እየተሸጡ ነው ሲሉ ፕሬዝዳንት ፑቲን ተናገሩ፡፡
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በሞስኮ በተካሄደ ውይይት ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር የሩሲያ ጦር መሳሪያዎች በዓለም ተፈላጊ ምርቶች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የአየር ላይ መቃወሚያ ጦር መሳሪያዎቻችን “እንደ ኬክ” እየተሸጡ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ ሀገሪቱ ከጦር መሳሪያ ሽያጭ ቢሊዮን ዶላሮችን ገቢ ማግኘቷን ተናግረዋል፡፡
በተለይም ዜድአርፒሲ የተሰኘው የአየር ላይ ጥቃቶች እንዳይሳኩ የሚያደርገው የጦር መሳሪያ በዓለም ላይ ያለው ተፈላጊነት ከፍተኛ እንደሆነም ተገልጿል፡፡
የሩሲያ ጦር መሳሪያዎች ከኔቶ ጋር ሲነጻጸሩ በብልጫቸው አይገናኙም ያሉት ፕሬዝዳንቱ ይህ አይደለም ዛሬ በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅትም ይህ ተቀይሮ አይውቅም ብለዋል፡፡
የጦር መሳሪያ ማምረቻ ፋብሪካዎች ከመቼውም ጊዜ በላይ ስራ በዝቶባቸዋል የተባለ ሲሆን ባለፉት ሁለት ዓመት ውስጥ ብቻ ፋብሪካዎቹ ከ520 ሺህ በላይ አዲስ ሰራተኞችን እንደቀጠሩ ተገልጿል፡፡
ፕሬዝዳንት ፑቲን አክለውም የሩሲያ ኢኮኖሚ አሁን ላይ ከአውሮፓ ሀገራት አንደኛ ከዓለም ደግሞ አምስተኛው ግዙፍ ኢኮኖሚ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
“አዲሶቹ ናዚዎች በዩክሬን ስልጣን ይዘው ሩሲያን እየወጉ ነው” ያሉት ፕሬዝዳንት ፑቲን ሁሉም ነገር ለድል በሚያበቃን መንገድ እየፈጸምን ነው ሲሉ በንግግራቸው ላይ ጠቅሰዋል፡፡
የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ሁለት ዓመት ሊሞላው ጥቂት ቀናት የቀሩት ሲሆን ሁለቱም ወገኖች ለአዲስ ዘመቻ ሀብት በማሰባሰብ ላይ ናቸው፡፡