ትራምፕ ሩሲያ የኔቶ አባል ሀገራትን እንድታጠቃ “እንደሚያበረታቱ” ተናገሩ
የቀድሞው ፕሬዝዳንት “ወንጀለኛ” ሲሉ የገለጿቸውን ለኔቶ በሚገባ የማያዋጡ ሀገራትን ነው ሞስኮ “እንዳሻት እንድታደርጋቸው” አበረታታለሁ ያሉት
ዋይትሃውስ በበኩሉ የዶናልድ ትራምፕ አስተያየት “አስደንጋጭና ወረራን የሚያበረታታ” ነው ብሎታል
የአሜሪካው የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሩሲያ ለኔቶ አመታዊ መዋጯቸውን በሚገባ የማይከፍሉ ሀገራትን እንድታጠቃ አበረታታለሁ አሉ።
ትራምፕ በሳውዝ ካሮሎና በምርጫ ቅስቀሳ ሲያደርጉ 31 አባል ያለውን ቡድን ተቀላቅለው ነገር ግን መዋጮ በሚገባ የማይከፍሉ ሀገራትን “ወንጀለኛ” ናቸው ሲሉ ተደምጠዋል።
በአንድ የኔቶ ስብሰባ ላይ ስማቸውን ካልጠቀሷቸው መሪ “መዋጮ ካልከፈልን እና በሩሲያ ከተወረርን ትከላከሉልናላችሁ?" የሚል ጥያቄ ተነስቶላቸው “አንዋጋላችሁም፤ እንደውም (ሩሲያ) የፈለገችውን እንድታደርግ አበረታታለሁ” ማለታቸውንም አውስተዋል።
የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን ድርጅት ኔቶ ከ2006 ጀምሮ አባል ሀገራቱ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርታቸው(ጂዲፒ) 2 በመቶውን ወታደራዊ ሃይላቸውን ማጠናከሪያ በጀት ለመያዝ ተስማምተዋል።
ስምምነቱ የወታደራዊ ጥምረቱን ለየትኛውም ጥቃት ዝግጁነትና አንዱ ለአንዱ ደራሽነት ያሳድጋል ተብሎ ቢጠበቅም የአሜሪካ አመታዊ በጀት ከቀሪዎቹ አባል ሀገራት ድምር የሚስተካከል ነው።
ይህም የአሜሪካን አመታዊ መዋጮ እንዲበዛ ማድረጉ የሚነገር ሲሆን፥ ሀገራቱ በ1949 ለተመሰረተው ኔቶ የሚያዋጡትን ክፍያ በመፈጸም ረገድም ተደጋጋሚ ወቀሳ ይቀርብባቸዋል።
የትራምፕ አስተያየትም ወታደራዊ በጀቷ ከ860 ቢሊየን ዶላር በላይ የሆነው አሜሪካ መዋጯቸውን በሚገባ የማይከፍሉ 30 ሀገራትን ከጥቃት የመከላከል ግዴታ የለባትም ያሉት ከዚህ በመነሳት ነው።
ዋይትሃውስ ግን የቀድሞው ፕሬዝዳንት አስተያየት “ያልተገራና አስደንጋጭ” ነው ብሏል።
የትራምፕ አስተያየት ወረራን የሚያበረታታና የአንዱ አባል ሀገር ወረራን እንደራሱ የሚመለከተውን የኔቶ መርህ የጣሰ ነው በሚልም ተቃውሞታል።
አወዛጋቢው የቀድሞ ፕሬዝዳንት በ2024ቱ የምርጫ ቅስቀሳቸው አስቀድሞም ሀገራቸውን ፍትሃዊ ላልሆነ ወጪ እየዳረገ ነው የሚሉትን ኔቶ አንዱ አጀንዳቸው አድርገውታል።