ፑቲን በኬርሰን እና ሉሃንስክ የሚገኙ ወታደሮችን ጎበኙ
ፕሬዝዳንቱ በሁለት ወራት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ያደረጉት ጉብኝት ወታደሮችን ለማበረታታት ያለመ ነው ተብሏል
ዩክሬን ከምዕራባውያን የጦር መሳሪያ ድጋፍ አሰባስባ ግዛቶቿን ለማስመለስ ዝግጅቷን ባጠናከረችበት ወቅት ነው ጉብኝት ያደረጉት
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በሞስኮ ቁጥጥር ስር በሚገኙ የዩክሬን ከተሞች ጉብኝት አካሄዱ።
በክሬምሊን የተለቀቀው ቪዲዮ ፕሬዝዳንቱ በሄሊኮፕተር በኬርሰን የሚገኙ የሩሲያ ወታደሮችን ሲጎበኙ ያሳያል።
ፑቲን በመቀጠልም በሉሃንስክ ግዛት የሚገኘውን የሩሲያ ጦር ማዘዣ መጎብኘታቸውን ምስሉ እንደሚያሳይ አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
የክሬምሊን ቃልአቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ፑቲን ኬርሰን እና ሉሃንስክን ትናንት መጎብኘታቸውን ገልጸዋል።
ፑቲን በሩሲያ ቁጥጥር ስር የሚገኙ አካባቢዎችን ሲጎበኙ በሁለት ወራት ውስጥ የትናንቱ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። ፑቲን ባለፈው ወር በማሪዮፖል ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል።
የጉብኝታቸው አላማ 14ኛ ወሩን በያዘው ጦርነት እየተሳተፉ የሚገኙ የሩሲያ ወታደሮችን ሞራል ከፍ ማድረግ ነው የተባለ ሲሆን፥ ከከፍተኛ መኮንኖችም ጋር መምከራቸውን የሩሲያ ቴሌቪዥን ዘግቧል።
ለወታደሮቹ የፋሲካ በዓል እንኳን አደረሳችሁ መልዕክት እና ስጦታ ማበርከታቸውንም ነው የዘገበው።
ኬርሰን እና ሉሃንስክ ከዶኔስክ እና ዛፓሮዥያ ጋር በህዝበ ውሳኔ ሩሲያን ለመቀላቀል የወሰኑ የዩክሬን ግዛቶች መሆናቸውን ሞስኮ ትገልጻለች፤ ዩክሬን እና ምዕራባውያን ግን ግልጽ ማጭበርበር ነው በሚል ይቃወሙታል።
አብዛኛው የዶኔስክ፣ ኬርሰን እና ዛፓሮዥያ ግዛት ክፍል አሁንም በዩክሬን ቁጥጥር ስር መሆናቸውን የሚጠቅሰው ሬውተርስ፥ ኬቭ የፕሬዝዳንት ፑቲን የትናንት ጉብኝት መቃወሟን ዘግቧል።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት አማካሪ ሚካሄሎ ፖዶልይካ “የዘር ጭፍጨፋ” ያወጁት ሰው በዩክሬን ምድር ጉብኝት ማድረግ የለባቸውም ማለታቸውን በመጥቀስ።
ፕሬዝዳንት ፑቲን በሉሃንስክ እና ኬርሰን ጉብኝት ያደረጉት ዩክሬን ከምዕራባውያን አጋሮቿ የጦር መሳሪያ ድጋፍ አሰባስባ ግዛቶቿን ለማስመለስ ዝግጅቷን ባጠናከረችበት ወቅት ነው።