ፕሬዝዳንት ፑቲንን በማሰር አሳልፎ የመስጠት ግዴታ ያለባቸው የአፍሪካ ሀገራት የትኞቹ ናቸው?
ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት በሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ላይ የእስር ማዘዣ አውጥቷል
33 የአፍሪካ ሀገራት የፍርድ ቤቱ አባል ሲሆኑ፤ ደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ፑቲንን የማሰር ግዴታ ውስጥ ገብታለች
የአለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ዳኞች በሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ላይ የእስር ማዘዣ ማውጣቱ ይታወሳል።
ይህንን ተከትሎም የአለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት አባል ሀገራት ፕሬዝዳንት ፑቲን ወደ ሀገራቸው ከገቡ አስሮ ለፍርድ ቤቱ አሳልፎ የመስጠት ግዴታ እንዳለባቸው ይታወቃል።
የአለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት አባልነትን የፈረሙ የዓለም ሀገራት 123 ሲሆኑ፤ ከእነዚህም ውስጥ 33 ሀገራት ከአፍሪካ መሆናቸው አሃዞች ያመለክታሉ።
አባል ከሆኑ የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ አንዷ የሆነችው ደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ፑቲን ወደ ደቡብ አፍሪካ ሊያቀኑ ይችላሉ መባሉን ተከትሎ አጣብቂኝ ውስጥ ገብታለች።
ፕሬዝዳንት ፑቲን የደቡብ አፍሪካ፣ ብራዚል፣ ቻይና፣ ሕንድ እና ሩሲያ ጥምረት የሆነው ብሪክስ የፊታችን ነሀሴ በፕሪቶሪያ በሚያደርገው ጉባኤው ላይ ይሳተፋሉ መባሉን ተከትሎ የእስር ማዘዣ ያወጣው የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ደቡብ አፍሪካ ህጉን እንድታከብር ጠይቋል።
ለመሆኑ ፕሬዝዳንት ፑቲንን በማሰር አሳልፎ የመስጠት ግዴታ ያለባቸው የአፍሪካ ሀገራት የትኞቹ ናቸው?
ሴኔጋል፣ ጋና፣ ማሊ፣ ሌሴቶ፣ ቦትስዋና፣ ሴራሊዮን፣ ጋቦን፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ናይጄሪያ፣ ሴንተራል አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ቤኒን፣ ሞሪሺየስ፣ ኒጀር፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ኡጋንዳ፣ ናሚቢያ እና ጋሚቢያ።
እንዲሁም ታንዛኒያ፣ ማላዊ፣ ጂቡቲ፣ ዛምቢያ፣ ጊኒ፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ኮንጎ፣ ላይቤሪያ፣ ኬንያ፣ ኮሞሮስ፣ ቻድ፣ ማዳካስካር፣ ሲሸልስ፣ ቱኒዚያ፣ ክፕቭርዴ እና ኮትዲቯር ናቸው።
ሀገራቱ በፈረሙት ስምምነት መሰረት በወንጀል የሚፈለግ ሰውን በማሰር አሳልፎ የመስጠት ግዴታ ያለባቸው ሲሆን፤ ጰሬዝዳንት ፑቲን ወደ እነዚህ ሀገራት ከሄዱ አስሮ አሳልፎ የመስጠት ግዴታ አለባቸው።
የአለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት አንድ ዓመት ባለፈው የዩክሬን ጦርነት የሩሲያ ጦር በፕሬዝዳንት ፑቲን ትዕዛዝ በንጹሀን ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደፈጸሙ በመግለጽ ነበር እስር ትእዛዝ ያወጣባቸው።
ሩሲያ በበኩሏ "የፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ረብ የለሽ እና የማይተገበር ነው፣ ሩሲያ ባልፈረመችው ህግ ማንም ሊጠይቃት አይችልም"በማለት ክሱን አጣጥላለች።