617 ሺህ ወታደሮች በዩክሬን እየተዋጉ ነው - ፑቲን
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት ካወጀች በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ለአለማቀፍ ጋዜጠኞች ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል
ኔቶ በበኩሉ ሩሲያ በዩክሬን ካሸነፈች ወረራዋ ይቀጥላል በሚል አስጠንቅቋል
በዩክሬን ሰላም የሚሰፍነው “አላማችን ስናሳካ ብቻ ነው” አሉ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን።
ፕሬዝዳንት ፑቲን ሩሲያ በየካቲት ወር 2022 በዩክሬን ላይ ጦርነት ካወጀች በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ለአለማቀፍ ጋዜጠኞች ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በኬቭ ሰላም የሚሰፍነው ግባችን ስናሳካ ብቻ ነው ያሉት ፑቲን፥ “የናዚ እሳቤን ማጥፋት፣ ትጥቅ ማስፈታት እና የሩሲያን ሉአላዊነት ማረጋገጥ” ዋና ዋና ግቦች መሆናቸውን አብራርተዋል።
ሩሲያ በአሁኑ ወቅት 617 ሺህ ወታደሮቿ በዩክሬን በውጊያ ላይ መሆናቸውንና ባለፈው አመት ለ300 ሺህ ተጠባባቂ ሃይሎች ጥሪ መደረጉን አስታውሰዋል።
ከ480 ሺህ በላይ ሩሲያውያን በበጎፈቃድ በውትድርና ለማገልገል መመዝገባቸውን ያነሱት ፑቲን፥ በዩክሬን ምን ያህል ወታደሮች እንደሞቱ ተጠይቀው ምላሽ ሳይሰጡ አልፈውታል።
የአሜሪካ የደህንነት መስሪያቤት ሪፖርት ግን በዩክሬን ከ315 ሺህ በላይ ሩሲያውያን መገደላቸውን ባለፈው ሳምንት ማመላከቱ የሚታወስ ነው።
ፕሬዝዳንት ፑቲን ከምዕራባውያን የጦር መሳሪያ ድጋፍ ለማግኘት በንጹሃን ዩክሬናውያን ላይ እየቆመረ ነው ያሉትን የዜለንስኪ አስተዳደርም ወቅሰዋል።
ፑቲን በሞስኮ መግለጫ በሚሰጡበት ስአት በተመሳሳይ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን ድርጅት ኔቶ ዋና ጸሃፊ የንስ ስቶልተንበግ፥ “ፑቲን በዩክሬን ካሸነፈ ወረራው በዚያ አይቆምም የሚል መግለጫ በብራሰልስ ሰጥተዋል።
ዩክሬን በሩሲያ የተያዙባትን ግዛቶች ለማስለቀቅ በሰኔ ወር ጀመርኩት ያለችው የመልሶ ማጥቃት በሚፈለገው ፍጥነት እየሄደ እንዳልሆነ ይነገራል።
ከሰሞኑ በአሜሪካ ጉብኝት ያደረጉት ፕሬዝዳንት ዜለንስኪ ምዕራባውያን ፈጣን ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው መጠየቃቸውም ይታወሳል።
የምዕራባውያን የኢኮኖሚ ማዕቀብና የፖለቲካ ማግለል እርምጃ ቢጠነክርም ሩሲያ በዩክሬን የምታካሂደውን “ወታደራዊ ዘመቻ” ከግቡ እስኪደርስ ድረስ እንደማታቆም ፕሬዝዳንት ፑቲን ተናግረዋል።