ፑቲን ለአምስተኛ የስልጣን ዘመን እንደሚወዳደሩ ተናገሩ
በመጋቢት 2024 በሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እስከ 2030 በስልጣን የሚያቆያቸውን ድምጽ እንደሚያገኙ ይጠበቃል
ፕሬዝዳንት ፑቲን ባለፉት 25 አመታት በሩሲያ ፖለቲካ ፊታውራሪ ሆነው ዘልቀዋል
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በመጋቢት ወር 2021 በሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንደሚፎካከሩ ተናገሩ።
ፑቲን በዩክሬን ጦርነት የጀግና ተግባር ለፈጸሙ ወታደሮች የማዕረግ ሽልማት ሲሰጡ ነው በቀጣዩ ምርጫ እንደሚፎካከሩ ለሁለት ወታደሮች መናገራቸው የተዘገበው።
ኮሎኔል አርትዮም ዦጋ የተባለ ወታደራዊ አዛዥ ፕሬዝዳንቱን በምርጫው እንደሚሳተፉ ጠይቋቸው ተሳትፏቸውን እንዳረጋገጡለትም ታስን ጨምሮ የተለያዩ የሩሲያ መገናኛ ብዙሃን እያስነበቡ ነው።
የ71 አመቱ ፕሬዝዳንት ለሶስት ቀናት በሚካሄደው ምርጫ ያለብርቱ ተቀናቃኝ መሳተፋቸው እንደማይቀር ቀደም ብዬ ዘግቤያለው ያለው ሬውተርስም፥ ፑቲን እስከ 2030 በስልጣን የሚያቆያቸውን ድምጽ እንደሚያገኙ ያለጥርጥር መግለጽ ይቻላል ብሏል።
ፑቲን ሶቪየት ህብረት ከተፈረካከሰች በኋላ የመጀመሪያው የሩሲያ ፕሬዝዳንት የነበሩትን ቦሪስ የልትሲን በ1999 ተክተው ወደ ክሬምሊን መዝለቃቸው ይታወሳል።
በ2000, 2004, 2012 እና 2018 በተካሄዱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫዎች ያሸነፉት ፑቲን በአምስተኛው የስልጣን ዘመን ምርጫም ድል እንደሚቀናቸው ይጠበቃል።
ከጆሴፍ ስታሊን በኋላ ሩሲያን ለረጅም ጊዜ ያስተዳደሩት ፑቲን በ2024 የሚደረገው ምርጫ የይስሙላ እንጂ አሸናፊነታቸው ቀድሞ የታወቀ ነው ይላሉ ተንታኞች።
ተቃዋሚዎቻቸውም ሞስኮ ዴሞክራሲያዊ ሀገር ለመምሰል የምታደርገው ምርጫ የአገዛዙን አምባገነንነት ሊሸፍነው አይችልም ይላሉ።
ደጋፊዎቻቸው ግን ፑቲን ከሶቪየት ህብረት በኋላ ገናናዋን ሩሲያ የፈጠሩት ፑቲን ናቸው፤ በቅርቡ የተደረገ የህዝብ አስተያየትም ፕሬዝዳንቱ ከ80 በመቶ በላይ ህዝብ እንደሚደግፋቸው አሳይቷል እያሉ ይከራከሩላቸዋል።
ፑቲን በምርጫው የሚያሰጋቸው ተፎካካሪ ባይኖርም ከሶስት አስርት በፊት እነሚካሄል ጎርቫቾቭ ከገጠማቸው ፈተና ያልተናነስ ከባድ ጫና አለባቸው።
ከዩክሬን ጋር የገቡበት ጦርነት ከ1962ቱ የኩባ የሚሳኤል ቀውስ በኋላ ከባዱ የምዕራባውያን ማዕቀብ በሞስኮ ላይ እንዲደራረብ አድርጎባቸዋል።
ጦርነቱ የሩሲያን ኢኮኖሚ በእጅጉ ቢፈትነውም መፍትሄም አላጡለትም፤ እንደ ቻይና ካሉ በምዕራባውያን ጫና ውስጥ ከሚገኙ ሀገራት ጋር ጥብቅ ትስስር በመፍጠር የፈተናውን ጊዜ እያለፉት ነው ይላሉ ተንታኞች።
ፑቲን እንደ ብሪክስ ያሉ ቡድኖችን ከማጠናከር ባለፈ በእስያ፣ በመካከለኛው ምስራቅ እና አፍሪካ ወዳጅ ሀገራትን በማፍራት ረገድም ውጤታማ መሆን መቻላቸው ይነሳል።
አምስተኛ የስልጣን ዘመናቸውም የአለማቀፉ ስርአት በአንድ ሀገር የበላይነት (አሜሪካ) መመራት የለበትም የሚለውን አቋማቸውን አጠናክረው የሚገፉበት እንደሚሆን ይጠበቃል።