ሩሲያ “ሳርማት” አህጉር አቋራጭ ሚሳዔልን በዓመቱ መጨረሻ ለውጊያ እንደምትጠቀም ፑቲን ገለጹ
ሩሲያ ሳርማት (አውሬው 2) ሚሳዔልን ከወራትበፊት መሞከሯ ይታወሳል
ሳርማት ሚሳዔል 15 የኒኩሌር አረሮችን የሚሸከም ሲሆን፤ እስከ 35 ሺህ ኪ.ሜ ርቀት ማጥቃት ይችላል
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሀገራቸው ሳርማት የተባለውን አህጉር አቋራጭ ሚሳዔል በያዝነው ዓመት ለውጊያ መጠቀም እንደምትጀምር አስታወቁ።
ፑቲን በዛሬው እለት ለተመረቁ ወታደራዊ ሰልጣኞች ባደረጉት ንግግር፤ ሩሲያ ያላትን ወታደራዊ አቅም የበለጠ እንምታጠናከር አረጋግጠዋል።
በዚህም ሀገራቸው በያዝነው የፈረንጆቹ 2022 መጨረሻ ላይ ሳርማት የተባለውን አህጉር አቋራጭ ሚሳዔል ለውጊያ እንደምታሰማራ አስታውቀዋል።
ሩሲያ ሩሲያ ሳርማት (አውሬው 2) ሚሳዔልን ባሳለፍነው መጋቢት ወር ላይ መሞከሯ ይታወሳል።
በሙከራው ወቅት የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን፤ “ሩሲያን ለመፈታተን የሚፈልጉ ጠላቶቻችን ቆም ብለው ሁለት ጊዜ እንዲያስቡ እናደርጋለን” ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።
እንዲሁም “ሳርማት” አህጉር አቋራጭ ሚሳዔል በእጅጉ የተለየ መሳሪያ መሆኑን እና ማንኛውም የሚሳዔል መከላከያ ስርዓቶችን የማለፍ አቅም ያለው መሆኑን ገልፀዋል።
አዲሱ የሩሲያ አህጉር አቋራጭ ሚሳዔል ሙከራ በደቡብ ምዕራብ ሩሲያ ከምትገኘው ፕሌስክ የተወነጨፈ ሲሆን፤ 6 ሺህ ኪሎ ሜትሮችን ከተጓዘ በኋላ በሌላኛው የሩሲያ አካል በሆነችው ሩቅ ምስራቅ ካማችታካ ማረፉ ይታወሳል።
የሩሲያ አህጉር አቋራጭ ባላስቲክ ሚሳዔል የቴክኒክና የታክቲክ ብቃታቸው ከፍተኛ እንዲሁም ዘመናዊ የሚሳዔል መከላከያ ስርዓቶችን መቋቋም የሚችል ነው ተብሏል።
“ሳርማት” አህጉር አቋራጭ ሚሳዔል 15 የኒኩሌር አረሮችን የሚሸከም ሲሆን፤ እስከ 35 ሺህ ኪ.ሜ ርቀት በመብረር ማጥቃት ይችላል።