ሩሲያ ባሳለፍነው ወር አሜሪካን መምታት የሚችል ሳርማት የተባለ አህጉር አቋራጭ ሚሳዔል ሞክራለች
ሩሲያ “ዚርኮን” የተባለ አዲስ ሃይፐርሶኒክ ክሩዝ ሚሳዔል የተሳካ ሙከራ ማድረጓን የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል።
አዲሱ የሩሲያ ዚርከን ሚሳዔል 1000 ኪሎ ሜትር ከተጓዘ በኋላ ኢላማውን መምታቱንም ሮይተርስ ይዞት በወወጣው ዘገባ አመላክቷል።
ሚሳዔሉ ከባሬንትስ ባህር ላይ የተተኮሰ ሲሆን፤ በነጭ ባህር ላይ የተቀመጠለትን ኢላማዉን መምታቱንም ነው የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ያስታወቀው።
የመከላከያ ሚኒስቴሩ በለቀቀው ቪዲዮ ላይ “ዚርኮን” የተባለው አዲሱ ሃይፐርሶኒክ ክሩዝ ሚሳዔል ከጦር መርከብ ላይ ሲወነጨፍም ያመለክታል።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን “ዚርኮን” ሀገሩቱ ከዚህ ቀደም ይፋ ሳታደርጋቸው ከቆየችው የአዲሱ ትውልድ የጦር መሳሪያዎች ውስጥ አንዱ ነው ብለዋል።
ሃይፐርሶኒክ ምንድን ነው፤ ሚሳዔሉን ከሌሎች ምን የተለየ ያደርገዋል
“ሃይፐርሶኒክ” የሚለው ቃል ከድምፅ በአምስት እጥፍ የሚፈጥን ማንኛውም ነገር የሚገልጽ ሲሆን፤ በሰዓት 6 ሺህ 174 ኪሎ ሜትር ወይም ከዚያ በላይ የሚበር፤ በሌላ አገላለጽ እጅግ በጣም ፈጣን የሚለውን ለመግለጽ ጥቅም ላይ ይውላል።
በዓለም ላይ ያሉ አብዛኞቹ ባላስቲክ ሚሳዔሎች ከድምፅ በአምስት እጥፍ የሚበልጥ ፍጥነት ያላቸው ሲሆን፤ ሃይፐርሶኒክ ሚሳዔሎችን ለየት የሚያደርጋቸው ግን ከምድር በጣም ርቀው አየር ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ የሚምዘገዘጉ መሆናቸው ነው።
እነዚህ አዳዲሶቹ ሚሳይሎች በሁለት አይነት መልክ የተሰሩ ሲሆን፤ የመጀመሪያው `ሃይፐርሶኒክ ግላይድ ተሸከርካሪ` የሚባልና የጠላትን ራዳር ለማታለል ተለያዩ እጥፋችን በመስራት የሚምዘገዘግ ነው
ሁለተኛው ደግሞ `ሃይፐርሶኒክ ክሩዝ ሚሳይል` (ኤች.ሲ.ኤም) ሲሆን፤ በጣም ፈጣን ባይሆንም ዝቅተኛ በሆነ ፍጥነት ለመብረር የተነደፈ እና ጠላት ራዳር ምላሽ መስጫ የሚሰጠው ጊዜ በጣም ጥቂት መሆኑ ይነገራል።
ሩሲያ ባሳለፍነው ወር የኒኩሌር አረር ተሸካሚ የሆነ እና አሜሪካን መምታት የሚችል አህጉር አቋራጭ ሃይፐርሶኒክ ሚሳዔል መሞከሯ ይታወሳል።
ሳርማት የሚል መጠሪያ ያለው አህጉር አቋራጭ ሃይፐርሶኒክ ሚሳዔሉ በአንድ ጊዜ እስከ 10 የኒኩሌር አረሮችን መሸከም የሚችል መሆኑ ይነገርለታል።