ሩሲያ አዲስ አህጉር አቋራጭ ባላስቲክ ሚሳዔል ሞከረች
“ስማርት” አህጉር አቋራጭ የባላስቲክ ሚሳዔሉ አንድ ጊዜ እስከ 10 የኒኩሌር አረር የመሸከም አቅም አለው
ፑቲን፤ “ሙከራው ለሩሲያ ጠላቶች ቆም ብለው እንዲያስቡ የሚያደርግ የቤት ስራን የሰጠ ነው” ብለዋል
ሩሲያ በአይነቱ ለየት ያለ አዲስ ስማርት አህጉር አቋራጭ የባላስቲክ ሚሳዔል ሙከራ ማደረጓን አስታወቀች።
አዲሱ የሩሲያ አህጉር አቋራጭ ሚሳዔል በደቡብ ምዕራብ ሩሲያ ከምትገኘው ፕሌስክ የተወነጨፈ ሲሆን፤ በሌላኛው የሩሲያ አካል በሆነችው ሩቅ ምስራቅ ካማችታካ ማረፉ ተነግሯል።
አህጉር አቋራጭ ባላስቲክ ሚሳዔሉ በአጠቃላይ 6 ሺህ ኪሎ ሜትሮችን እንደተጓዘም ነው የተገለፀው
አዲሱ የሩሲያ ባላስቲክ ሚሳዔል የቴክኒክና የታክቲክ ብቃታቸው ከፍተኛ እንዲሁም ዘመናዊ የሚሳዔል መከላከያ ስርዓቶችን መቋቋም የሚችል ነው ተብሏል።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን፤ “ሚሳዔሉ እስካሁን ካሉት የተለየ መሳሪያ ነው፤ የሰራዊታችንን የመዋጋት አቅም ያሳድጋል” ያሉ ሲሆን፤ “በአስተማማኝ ሁኔታ ሩሲያን ከውጭ አደጋዎች መከላከል እንዲሁም ሩሲያን ለማስፈራራት ለሚሞክሩም በቂ ምለሽ ለመስጠት የሚያስችል ነው” ብለዋል።
“ሙከራው ለሩሲያ ጠላቶች ቆም ብለው እንዲያስቡ የሚያደርግ የቤት ስራን የሰጠ ነው” ሲሉም ፕሬዝዳንት ፑቲን አስታውቀዋል።
የዓለም አቀፉ የስትራቴጂክ ጥናት ማእከል የኤሮስፔስ ባለሙያ የሆኑት ዶጉላስ ባሪ፤ ሩሲያ አዲስ ያደረገችው ሙከራ ለሀገሪቱ አዲስ የስኬት መንገድ መሆኑን አስታውቀዋል።
ሩሲያ ሚሳዔሎችን በስራ ላይ ለማዋል ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ማድረግ ይጠበቅባታል ያሉት ባሪ፤ አዳዲሱቹ ሚሳዔሎች ስራ ላይ ሲውሉ SS-18 እና SS-19 የተባሉ እድሜ ጠገብ የሩሲያ ሚሳዔሎችን ይተካሉ ብለዋል።
ስማርት የተባለው አዲሱ ሩሲያ ሚሳዔል በአንድ ጊዜ እስከ 10 የኒኩሌር አረር የመሸከም አቅም እንዳላቸውም ባለሙያው ተናግረዋል።