ሩሲያ አዲስ የሞከረችውን ሳርማት አህጉር አቋራጭ የባላስቲክ ሚሳዔል “ላሰማራ ነው” አለች
ሳርማት ሚሳዔል 15 የኒኩሌር አረሮችን የሚሸከም ሲሆን፤ እስከ 35 ሺህ ኪ.ሜ ርቀት ማጥቃት ይችላል
ሚሳዔሉ ለሚቀጥሉት 30-40 ዓመታት የሩሲያ ልጆችና የልጅ ልጆች ደህንነት ዋስትና የሚያረጋግጥ ነው ተብሏል
ሩሲያ ባሳለፍነው ሳምንት የሞከረችውን አዲሱን “ሳርማት” የተባለ የኒኩልር አህጉር አቋራጭ የባላስቲክ ሚሳዔል ልታሰማራ መሆኑን አስታውቃለች።
ሩሲያ አዲሱን የሳርማት የኒኩሌር አህጉር አቋራጭ የባላስቲክ ሚሳዔል በዚህ ክረምት ወደ ውጊያ ስራ ልታሰማራ ማቀዷን ገልጻለች።
ሳርማት አህጉር አቋራጭ የባላስቲክ ሚሳዔል ከሞስኮ በስተምስራቅ 3 ሺህ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው በክራስኖያርስክ ግዛት ውስጥ በምትገኘው ኡዙር ስፍራላይ እንደሚተከልም ታስ ዘግቧል።
የሮስኮሞርስ ስፔስ ኤጀንሲ ዳይሬክተር ዲሜትሪ ሬጎዚን፤ አዲሱን የሳርማት የኒኩልር አህጉር አቋራጭ የባላስቲክ በቀጣይ የክረምት ወራት መግቢያ ላይ ለማሰማራት አስበናል ብለዋል።
ሩሲያ የሳርማት የኒኩሌር አህጉር አቋራጭ ሙከራ ደረገችበት እለት ታሪካዊ ነው ያሉት ዲሜትሪ ሬጎዚን፤ “ሚሳዔሉ ለሚቀጥሉት 30-40 ዓመታት የሩሲያ ልጆችና የልጅ ልጆች ደህንነት ዋስትና የሚያረጋግጥ ነው” ብለዋል።
ሩሲያ ባለፈው ረቡዕ ሳርማት የተባለውን አህጉር አቋራጭ ባላስቲክ ሚሳኤል የተሳካ ሙከራ ማድረጓ ይታወሳል።
አዲሱ የሩሲያ አህጉር አቋራጭ ሚሳዔል በደቡብ ምዕራብ ሩሲያ ከምትገኘው ፕሌስክ የተወነጨፈ ሲሆን፤ 6 ሺህ ኪሎ ሜትሮችን ከተጓዘ በኋላ በሌላኛው የሩሲያ አካል በሆነችው ሩቅ ምስራቅ ካማችታካ ማረፉ ተነግሯል።
አዲሱ የሩሲያ ባላስቲክ ሚሳዔል የቴክኒክና የታክቲክ ብቃታቸው ከፍተኛ እንዲሁም ዘመናዊ የሚሳዔል መከላከያ ስርዓቶችን መቋቋም የሚችል ነው ተብሏል።
“ሳርማት” አህጉር አቋራጭ ሚሳዔል 15 የኒኩሌር አረሮችን የሚሸከም ሲሆን፤ እስከ 35 ሺህ ኪ.ሜ ርቀት በመብረር ማጥቃት ይችላል።