ቭላድሚር ፑቲን በጥቁር ባህር ምክንያት ከኔቶ ጋር መካረር ውስጥ መግባት አያስፈልግም አሉ
ፑቲን የመከላከያ ኃይላቸው በጥቁር ባህር ልምምድ ለማድረግ ቢያስብም ውድቅ አድርገውታል
አሜሪካ በበኩሏ የጦር መርከቦቿ በጥቁር ባህር ከኔቶ ጋር ተባብራ እየሰራች እንደሆነ ገልጻለች
የሩሲው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በጥቁር ባህር አካባቢ ባለው ሁኔታ ከሰሜን ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ጋር መካረር ውስጥ መግባት እንደማይገባ አስታወቁ።
ፑቲን ትናንትና ባደረጉት ቃለ መጠይቅ በጥቁር ባህር አካባቢ ባለው ሁኔታ እሰጥ አገባ ውስጥ መግባት አስፈላጊ እንዳልሆነ ገልጸዋል።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር በጥቁር ባህር አካባቢ ወታደራዊ ልምምድ በማድረግ የኔቶን ጫና ለመቋቋም ያለመ ዕቅድ አዘጋጅቶ የነበረ ቢሆንም ፑቲን ይህንን ውድቅ ማድረጋቸው ተሰምቷል። ፕሬዝዳንቱ እራሳቸው በአካባቢው ውጥረት እንዲነግስ እንደማይፈልጉም ገልጸዋል።
ቀደም ሲል ሞስኮ በአካባቢው የዋሸንግተንና አጋሮቿ እንቅስቃሴ እንዳሰጋት ስትገልጽ መቆየቷ ይታወሳል። በጥቁር ባህር አካባቢ የምዕራባውያን የስለላ አውሮፕላኖች እንቅስቃሴ፤ የስትራቴጂያዊ ቦምቦችን የያዙ አውሮፕላኖች በረራ እንዲሁም የአሜሪካ የጦር መርከቦች በአካባቢው መገኘትን ሩሲያ እንደ ስጋት ስታየው ነበር።
አንዳንዶቹ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ያሉት በክሬሚያ አቅራቢያ መሆኑንም ሞስኮ ስትገልጽ መቆየቷን ሲ.ጂ.ቲ.ኤን ዘግቧል።
ፑቲን የመከላከያ ሃይላቸው በጥቁር ባህር ልምምድ ለማድረግ ቢያስብም ምቹ እና ዓላማን ማሳኪያ እንዳልሆነ ገልጸዋል።
በአካባቢው ያለውን ሁኔታ ማጋጋል እንደማያስፈልግ የገለጹት ፑቲን የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴርም በአካባቢው ያለው እንቅስቃሴ የተወሰነ እንዲሆን አድርጓል ብለዋል።
አሜሪካ በበኩሏ የጦር መርከቦቿ በጥቁር ባህር ከኔቶ ጋር ተባብራ እየሰራች እንደሆነ ገልጻለች። የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንም አሜሪካና አጋሮቿ በጥቁር ባህር ያልታቀደ ወታደራዊ ልምምድ እያደረጉ መሆኗን ከሩሲያ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል።
ዋሸንግተንና አጋሮቿ በአካባቢው የሚያደርጉት ያልታቀደ ወታደራዊ ልምምድ ከፍተኛ ፈተና እንደሆነባቸው ገልጸዋል። ሞስኮ የቤላሩስና የአውሮፓ ሕብረት ስደተኞችን ጉዳይ ለመፍታትም ዝግጁ መሆኗን ፑቲን ተናግረዋል።