ቱርክ፣ ኢራን እና ሩሲያ በሶሪያ ጉዳይ በዶሃ ሊወያዩ መሆኑ ተገለጸ
አማጺያኑ የሶሪያ የእርስበርስ ጦርነት ከተጀመረ ከ13 አመታት በኋላ በጦር ሜዳ ከፍተኛ ድል በመጎናጸፍ፣ በበሽር አላሳድ አገዛዝ ላይ ከፍተኛ ኪሳራ አድርሰዋል

አማጺያኑ አሌፖ እና ሀማ የተባሉ ሁለት ከተሞችን የአሳድ ኃይሎችን በማስለቀቅ ተቆጣጥረዋል
ቱርክ፣ ኢራን እና ሩሲያ በሶሪያ ጉዳይ በዶሃ ሊወያዩ መሆኑ ተገለጸ።
የቱርክ፣ የኢራን እና የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች መብረቃዊ በሆነው የሶሪያ አማጺያን ግስጋሴ ጉዳይ በነገው እለት በኳታር ዶሃ ተገናኝተው እንደሚወያዩ ሮይተርስ ዘግቧል።
አማጺያኑ የሶሪያ የእርስበርስ ጦርነት ከተጀመረ ከ13 አመታት በኋላ በጦር ሜዳ ከፍተኛ ድል በመጎናጸፍ፣ በበሽር አላሳድ አገዛዝ ላይ ከፍተኛ ኪሳራ አድርሰዋል።
ለበርካታ አመታት በሀገሪቱ ሰሜን ምዕራብ ክፍል ለበርካታ አመታት መሽገው የነበሩት አማጺያኑ በሀያት ታህሪር አል ሻምበ በተባለው ቡድን በመመራት ባለፈው ሳምንት የሶሪያን ትልቅ ከተማ አሌፖን ተቆጣጥረው በደቡብ በኩል ወደ ሀማ ከተማ መግፋት ችለው ነበር። አማጺያኑ በትናንትናው እለት ደግሞ ሁለተኛዋን ትልቅ ከተማ ሀማን ተቆጣጥረዋል።
ቱርክ፣ ሩሲያ እና ኢራን 'አስታና ፒስ ፕሮሰስ' በተባለ ማዕቀፍ በሶሪያ የወደፊት እጣፊንታ ላይ የሶስትዮሽ ምክክር ያደርጋሉ። የኔቶ አባሏ ቱርክ ተቃዋሚዎችን የምትደግፍ ሲሆን ሩሲያ እና ኢራን ደግሞ የአሳድ አገዛዝን እንደሚደግፉ ይገለጻል።
ሮይተርስ ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ ሶስት ሚኒስትሮች ከዶሃ ፎረም ጎንለጎን በነገው እለት ይገናኛሉ።
ባለፈው ሰኞ እለት የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሀካን ፊዳን ከኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አርቃች ጋር ንግግር ካደረጉ በኋላ የአስታና ሂደትን የመጀመር አዲስ ጥረት እንደሚካሄድ ተናግረዋል።
አዲሱ የሶሪያ ግጭት ከተጀመረ ወዲህ አንካራ የአሳድ አገዛዝ ከሶሪያ ህዝብ ጋር መክሮ ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲፈልግ ጥሪ ስታቀርብ ነበር። በአማጺያኑ እንቅስቃሴ ውስጥ እጇ የለበትም ያለችው አንካራ አዲስ የተፈናቃዮች ማዕበል ማየት እንደማትፈልግ ገልጻለች።