ሩሲያ ከዩክሬን ባሻገር በሌሎች ሀገራት ጦርነት ለመክፈት አስባለች?
ፕሬዝዳንት ፑቲን ሞስኮ በፖላንድ፣ ቼክ ሪፐብሊክ እና በባልቲክ ሀገራት ላይ ጦርነት ልታውጅ ትችላለው ወይ ተብለው ተጠይቀው ምላሽ ሰጥተዋል
ፑቲን ለዩክሬን ኤፍ-16 ጄቶችን የሚሰጡ ሀገራትንም አስጠንቅቀዋል
ሩሲያ በፖላንድም ሆነ በሌሎች የኔቶ አባል ሀገራት ላይ ጦርነት መክፈት እንደማትፈልግ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ተናገሩ።
ፕሬዝዳንቱ አሜሪካ መራሹ ወታደራዊ ጥምረት ኔቶ ከሶቪየት ህብረት መፈራረስ በኋላ የሚያደርገው መስፋፋት አሳሳቢ ቢሆንም ሞስኮ የኔቶ አባል ሀገራትን ለማጥቃት አላሰበችም ብለዋል።
ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት ከከፈተች በኋላ እንደ ፖላንድ፣ ኢስቶኒያ፣ ላቲቪያ እና ሊቱኒያ ያሉ ሀገራት የኬቭ እጣ ፈንታ ይደርሰናል የሚል ስጋት እንዳደረባቸው ይታወቃል።
የኔቶ አባል የሆኑት ሀገራቱ ለዩክሬን ወታደራዊ ድጋፍ ከማድረግ ባሻገር መሸጋገሪያ ድልድይ መሆናቸውም በኬቭ ኔቶን እየተፋለምኩት ነው ለምትለው ሞስኮ በበጎ የሚታይ አይደለም።
ፖላንድና የባልቲክ ሀገራት ሩሲያ ወረራ ልትፈጽምብን ትችላለች የሚለውን ስጋታቸውን ደጋግመው ቢያነሱም ፕሬዝዳንት ፑቲን ሀገራቱን የመውጋት ምንም አይነት እቅድ የለንም ብለዋል።
ከሩሲያ አየር ሃይል አብራሪዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ከኔቶ አባል ሀገራት ጋር ጦርነት ውስጥ ሊያስገባ የሚችለውን ጉዳይ ግን አልሸሸጉም።
ዩክሬን ከሁለት አመት በላይ ያስቆጠረው ጦርነት እንዲጓተት ካደረጉ ምክንያቶች አንዱ የአየር ሃይል የበላይነት አለመያዟ በምክንያትነት ይጠቀሳል።
ድሮኖችን በስፋት መጠቀም ብትችልም በጦርነቱ በርካታ የጦር አውሮፕላኖቿ ወድመዋል።
የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲሚትሮ ኩሌባ አሜሪካ ሰራሹን ኤፍ - 16 ጄት ለመስጠት ቃል የገቡ ሀገራት በቀጣይ ወራት ውስጥ ሊልኩልን ይገባል ማለታቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
ቤልጂየም፣ ዴንማርክ፣ ኖርዌይ እና ኔዘርላንድስ ለዩክሬን ኤፍ - 16 ተዋጊ ጄቶችን ለመስጠት ቃል ገብተዋል፤ በርካታ ሀገራትም የዩክሬን አብራሪዎችን ለማሰልጠን ጥምረት ፈጥረዋል።
ፕሬዝዳንት ፑቲን ሀገራቸው ኤፍ-16 ጄቶቹን መትታ በመጣል በአውደ ውጊያው ላይ ተጽዕኖ እንደማይኖራቸው ታደርጋለች ሲሉ ተደምጠዋል።
ኤፍ - 16 ጄቶቹ የኒዩክሌር መሳሪያዎችን መሸከም የሚችሉ ናቸው።
“እነዚህ አውሮፕላኖች ከዩክሬን ውጭ የኒዩክሌር መሳሪያዎችን ከተኮሱ ሀገራቱ ህጋዊ ኢላማችን ይሆናሉ፤ የትም ቦታ ቢሆኑ ጥቃት ይከፈትባቸዋል” ሲሉ ጦርነቱ ከዩክሬን ሊሻገር የሚችልበትን ሁኔታ አብራርተዋል።