ሩሲያ ለዩክሬን ያስወነጨፈችው ክሩዝ ሚሳይል የፖላንድን የአየር ክልል መጣሱ ተነገረ
የፖላንድ ጦር ቃል አቀባይ ጃሴክ ጎሪዊስኪይ ሚሳይሉ ወደ ዩክሬን ከመመለሱ በፊት በፖላንድ የአየር ክልል ውስጥ ሁለት ኪሎሜትር መጓዙን ተናግረዋል
ሩሲያ በዩክሬን ዋና ከተማ እና በምዕራባዊ ሊቪቭ ከተማ የሚገኙ ወሳኝ መሰረተ ልማቶችን በሚሳይል መምታቷን ኪቭ አስታውቃለች
ሩሲያ ለዩክሬን ያስወነጨፈችው ሚሳይል የፖላንድን የአየር ክልል መጣሱ ተነገረ።
ሩሲያ በዩክሬን ዋና ከተማ እና በምዕራባዊ ሊቪቭ ከተማ የሚገኙ ወሳኝ መሰረተ ልማቶችን በሚሳይል መምታቷን ኪቭ አስታውቃለች።
ዋርሶው እንዳለችው ከሆነ በዚህ ጥቃት ከተወነጨፉት የሩሲያ ሚሳይሎች ውስጥ አንደኛው የፖላንድን የአየር ክልል ጥሷል።
የፖላንድ ጦር ቃል አቀባይ ጃሴክ ጎሪዊስኪይ ሚሳይሉ ወደ ዩክሬን ከመመለሱ በፊት በፖላንድ የአየር ክልል ውስጥ ሁለት ኪሎሜትር መጓዙን ተናግረዋል።
ሞስኮ ለሁለት አመት በዘለቀው የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ውስጥ በዩክሬን የኃይል መሰረተ ልማት ላይ ከባድ የሚባል ጥቃት ካደረሰች ከሁለት ቀን በኋላ ነው በኪቭ ላይ 57 የሚሳይል እና የድሮን ናዳ ያዘነበችው።
የሌቪቭ ክልል ገዥ ማክሲም ኮዚስኪ በቴሌግራም ገጻቸው ላይ "ወራሪዎች በመጀመሪያዎቹ ሚሳይሎች ሁለት ወሳኝ መሰረተልማቶችን መትተዋል" ብለዋል።
ጥቃቱ የደረሰው መትቶ ለመጣል አስቸጋሪ በሆነው ኪንዝል ሚሳይል የተፈጸመ ነው ያሉት ገዥው ኢላማ የተደረገው መሰረተልማት ምን እንደሆነ ግለጽ አላደረጉም።
የኢነርጁ ሚኒስትሩም በሌቪቭ ወሳኝ የኃይል መሰረተ ልማት መመታቱን እና ኃይል መቋረጡን ተናግረዋል። ሚኒስትሩ እና ገዥው እያወሩ ያሉት ስለአንድ መሰረተልማት ስለመሆኑ አልታወቀም።
የዩክሬን አየር ኃይል ከ29ኙ ሚሳይል ውስጥ 18ቱን ከ28ቱ ድሮኖች ውስጥ 25ቱን መትቶ ማውደሙን አስታውቋል።
የተጎዳው መሰረተ ልማት ምን እንደሆነ ባይታወቅም ባለፈው አርብ እለት ባደረሰችው ድብደባ ኃይል እንዲቋረጥ ያደረገችው ሩሲያ በኃይል መሰረተ ልማት ላይ እያደረሰች ያለውን ጥቃት አጠናክራ ቀጥላለች።
በኃይል መሰረተልማቱ ላይ ጥቃት ከደረሰ በኋላ ኃይል ወደ ውጭ ትልክ የነበረችው ዩክሬን ከእሁድ ጀምሮ ወደ ውጭ መላኳን ማቆሟን የኢነርጂ ሚኒስቴሩ ገልጿል።
የዩክሬን አየር ኃይል በርካታ ሚሳይሎችን ሲያከሽፍ በኪቭ አየር ላይ ከፍተኛ ፍንዳታ መፈጠሩን የኪቭ ወታደራዊ አስተዳደሪ ሰርሂይ ፖፕኮ ተናግረዋል።
አስተዳዳሪው እንደገለጹት በኪብ በነበረው ጥቃት የደረሰው ጉዳት አነስተኛ ነው።
ሩሲያ ላለፉት ሁለት አመት በዩክሬን ያወጀችውን "ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ" አሁን ላይ ምዕራባውያን እየተሳተፉ ስለሆነ "ጦርነት" የሚል ስያሜ ሰጥታዋለች።
የክሬሚሊን ቃል አቀባይ ዲሜትሪ ፔስኮፕ ባለፈው አርብ እለት የሰጡት አስተያየት ለዩክሬን እና ለምዕራባውያን ጆሮ የሚስብ ላይሆን ይችላል። ነገርግን ሩሲያ ውስጥ ላለፉት ሁለት አመታት ጦርነቱን "ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ" እያሉ እንዲጠሩ ሲነገራቸው የነበሩት ሰዎች የግጭቱ ሁኔታ መቀየሩን እና ተጨማሪ መስዋትነት የሚጠበቅባቸው መሆኑን እንዲያውቁ ለማድረግ ነው።
ሞስኮ ይህን ጥቃት እያደረሰች ያለችው ዩክሬን በሩሲያ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ወቅት ያደረሰችውን ጥቃት ለመበቀል እንደሆነ ይታመናል።
ጦርነት የሚለውን ቃል ላለመጠቀም ለረጅም ጊዜ ጥንቃቄ ሲያደርጉ የነበሩት ከፑቲን በተዋረድ ያሉት ባለስልጣናትም አሁን ላይ ጦርነት እያሉ መናገር ጀምረዋል።
ሩሲያ በከፊል የወረረቻቸውን አራት የምራቅ ዩክሬን ግዛቶች ሙሉ በሙሉ ለመጠቅለል ጦርነቱን እንደምትቀጥል ገልጻለች።