ሩሲያ ደህንነቷን ለማስከበር ስትል ተጨማሪ ግዛቶችን ከዩክሬን ልትወስድ ትችላለች ተብሏል
ፕሬዝዳንት ፑቲን ሶስተኛው የዓለም ጦርነት ሊነሳ ጫፍ ላይ መድረሱን ተናገሩ፡፡
ሩሲያን ለቀጣዮቹ ስድስት ዓመታ በፕሬዝዳንትነት እንዲመሩ የተመረጡት ቭላድሚር ፑቲን ሶስተኛ ዓለም ጦርነት ሊጀመር ጫፍ ደረጃ ለይ መድረሱን ተናግረዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ፑቲን ምርጫውን ማሸነፋቸውን ተከትሎ ባደረጉት ንግግር ሩሲያ አሜሪካ ከሚመራው ኔቶ ጋር የቀጥታ ጦርነት ለመግጠም የመጨረሻ ደረጃ ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ይህ ጦርነት ከተጀመረ ደግሞ ሶስተኛው የዓለም ጦርነት ይጀመራል ያሉት ፕሬዝዳንት ፑቲን ሩሲያ ይህ እንዳይሆን ፍላጎቷ መሆኑን በንግግራቸው ላይ ጠቅሰዋል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ከሁለት ሳምንት በፊት ወታደሮቿን ወደ ዩክሬን ልትልክ እንደምትችል ከተናገሩ በኋላ ኔቶን ጨምሮ በርካታ ሀገራት ሀሳቡን ውድቅ አድርገውታል፡፡
በሩሲያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ቭላድሚር ፑቲን በከፍተኛ ድምጽ አሸነፉ
ሩሲያ ከዩክሬን ጦርነት መጀመሯን ተከትሎ በ1962 ከተከሰተው የኩባ ሚሳኤል ቀውስ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከምዕራባዊያን ሀገራት ጋር ቅራኔ ውስጥ ትገኛለች፡፡
ንግግር በሚደርጉበት ወቅት ከኔቶ ጋር ጦርነት ለመግጠም ዝግጁ ኖት በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም “ባለንበት ዘመናዊ ዓለም ውስጥ የማይቻል ነገር የለም” ሲሉ ፕሬዝዳንት ፑቲን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ አክለውም የኔቶ ወታደሮች በዩክሬን እንዳሉ እናውቃለን፣ ሩሲያ እነዚህን ወታደሮች በዩክሬን እየገደለቻቸው ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፤
ዩክሬን ሩሲያን ማጥቃቷን ከቀጠለች ለደህንነታችን ስንል ተጨማሪ መሬቶችን ከዩክሬን ሊቀሙ እንደሚችሉም ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ማክሮን ጦርነቱን ከሚያባብስ አስተያየት ቢቆጠቡ ጥሩ ነው ያሉት ፕሬዝዳንት ፑቲን አሁንም ያንን ለማድረግ ጊዜው አልረፈደም ብለዋል፡፡
ለአንድ ሳምንት በሚል የተጀመረው የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ሶስተኛ ዓመቱ ላይ የሚገኝ ሲሆን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች ከሁለቱም ወገን እንደሞቱ ሲገለጽ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደግሞ ለስደት ተዳርገዋል፡፡