ዶናልድ ትራምፕ በ2020ው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ጣልቃ በመግባት የተለያዩ ክሶች እየቀረበባቸው ነው
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከነገ በስቲያ ሀሙስ በጆርጂያ ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ ተናግረዋል።
ዶናልድ ትራምፕ ከሶስት አመት በፊት በተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በጆርጂያ ግዛት ድምፅ ለማጭበርበር ሞክረዋል በሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።
ጉዳያቸውን በውጭ ሆነው እንዲከታተሉ የ200 ሺህ ዶላር ዋስትና እንዲያቀርቡ ታዘዋል።
በትራምፕ ላይ 13 ክሶችን ያቀረቡት የፉልተን ካውንቲ አቃቤህግ ፋኒ ዊሊስ እና የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጠበቆች ስምምነት ተፈራርመዋል።
በዚህም ትራምፕ በምስክሮች ላይ ጫና ለማሳደርና ለማስፈራራት እስካልሞከሩ ድረስ ክሳቸውን በውጭ ሆነው መከታተል እንደሚችሉም ነው የተገለፀው።
በማህበራዊ ሚዲያዎችም ክሱን እና ምስክሮችን የተመለከቱ መረጃዎችን እንዳያጋሩም ተስማምተዋል።
አወዛጋቢው የቀድሞው ፕሬዝዳንት ግን "ትሩዝ ሶሻል" በተሰኘው ማህበራዊ ትስስር ገፃቸው፥ ክስ የመሰረተችባቸውን አቃቤ ህግ ፋኒ ዊሊስ "ግራ ዘመም አክራሪ" በማለት ሲወርፉ ጊዜ አልወሰደባቸውም።
በዚህ አመት አራት የወንጀል ክስ የቀረበባቸው ዶናልድ ትራምፕ ክሶቹ ፖለቲካዊ ፍላጎት የተጫናቸው እንደሆኑ ይገልፃሉ።
በቀጣዩ አመት በሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ተቀባይነታቸውን ለማሳጣት ክሶች እየተደራረቡባቸው ሲናገሩም ይደመጣል።
በጆርጂያም ከነገ በስቲያ ፍርድ ቤት የሚቀርቡ መሆናቸውን ተከትሎ በነገው እለት የሚካሄድ የሪፐብሊካኖች የቴሌቪዥን የምርጫ ክርክር ያልፋቸዋል።
የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላት የ2024ቱን እጩ ተፎካካሪ በቀጣዩ አመት ጥር ወር የሚመርጡ ሲሆን ትራምፕ የቀረቡባቸው ክሶች አሉታዊ ተፅዕኖ ያደርሱባቸዋል ተብሏል።