“በምስራቃዊ ዩክሬን የምናደርገውን ግስጋሴ የሚያስቆም አልተገኘም” - ፑቲን
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ዩክሬን በኩርስክ ክልል ዘልቃ መግባቷ ሃይሏን አዳከመ እንጂ የፈየደላት ነገር የለም ብለዋል
የዩክሬን ጦር ወደ ሩሲያ ግዛት ዘልቆ ከገባ ነገ አንድ ወር ይደፍናል
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሀገራቸው በምስራቃዊ ዩክሬን ተጨማሪ ይዞታዎችን መቆጣጠሯን ገለጹ።
ፕሬዝዳንት ፑቲን በቭላዲቮስቶክ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው ኢስተርን ኢኮኖሚክ ፎረም ላይ ባደረጉት ንግግር ዩክሬን በሩሲያዋ ኩርስክ ክልል ዘልቃ ገብታ ጥቃት ማድረሷ ሞስኮ በምስራቃዊ ዩክሬን የምታደርገውን ግስጋሴ ማስቆም አልቻለም ብለዋል።
ኬቭ በኩርስክ መግባቷ ወሳኝ ወታደራዊ ሃይሏን እያሳጣት መሆኑንና በአንጻሩ ሩሲያ በምስራቃዊ ዶንባስ ክልል ተጨማሪ ይዞታዎችን እንድትቆጣጠር ማስቻሉን ነው ፑቲን ያነሱት።
“የጠላት (ዩክሬን) አላማ ተደናግጠን በወሳኝ ስፍራዎች ጦርነት እንድናቆምና ከሌሎች አካባቢዎች ወደ ኩርስክ ወታደሮችን እንድናሰማራ ነበር፤ ግን አልተሳካም” ብለዋል።
የሩሲያ ወታደሮች ከአንድ ወር በፊት የሀገራቸውን ድንበር ጥሶ የገባውን የዩክሬን ጦር ለማስወጣት “ቅዱስ ግዳጅ” ተሰጥቷቸዋል ሲሉ መደመጣቸውንም ሬውተርስ ዘግቧል።
የዩክሬን ጦር አዛዥ ኦሌክሳንደ ሲይርስኪ ግን የኩርስክ ዘመቻ ክሬምሊንን ማስደንገጡን ገልጸዋል።
ፑቲን እና የሩሲያ ሹማምንት በበኩላቸው ኬቭ ሁለት አመት ባለፈው ጦርነት ትልቁ የታክቲክ ስህተት መሆኑን ተናግረዋል።
ለሩሲያ ጦርነትን ወደ ራሷ ግዛት ወስደንላታል ያሉት የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ ጦራቸው በኩርስክ ክልል ይዞታውን አስፋፍቶ በቀጣይ ከሞስኮ የሚቃጣበትን ጥቃት ለመከላከል ምሽግ እንደሚገነባ መናገራቸው የሚታወስ ነው።
የሩሲያው አቻቸው ፑቲን ግን ቁጥራቸውን ያልጠቀሷቸው የዩክሬን ወታደሮች ተደምስሰው ከኩርስክ ክልል እየወጡ መሆኑን ነው በቭላዲቮስቶክ እየተካሄደ ባለው ፎረም ላይ ያብራሩት።
“በምስራቃዊ ዩክሬን የምናደርገውን ግስጋሴ የሚያስቆመን አንዳች ሀይል አልተገኘም” ማለታቸውም ተዘግቧል።
ኬቭ በ2023 ላይ እጀምረዋለው ያለችው የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ ሳይሳካ መቅረቱን ተከትሎ ሞስኮ በምስራቃዊ ዩክሬን ተጨማሪ ግዛቶችን እየተቆጣጠረች ነው።
የዩክሬንን 18 በመቶ መሬት የተቆጣጠረችው ሩሲያ ወቅታዊው የኩርስክ ዘመቻ ከኬቭ ጋር ለድርድር የሚያስቀጥ አይደለም ብላለች።
ፑቲን ቻይና፣ ህንድ እና ብራዚል ሀገራቱን ሊያደራድሩ እንደሚችሉና በጦርነቱ መጀመሪያ አካባቢ በቱርክ ኢስታንቡል ስምምነት ተደርሶባቸው የነበሩ ጉዳዮች የንግግር መነሻ መሆን እንደሚችሉ ገልጸዋል።