የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር በገዛ ፈቃዳቸው ከስልጣን ለቀቁ
የዩክሬን ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር እና ሶስት ሚንስትሮች ከሰሞኑ ስልጣን መልቀቃቸው ይታወሳል
ዘለንስኪ ያጋጠማቸውን የካቢኔ ክፍተት ለመሙላት አዳዲስ ሹመቶችን እንደሚሰጡ ይጠበቃል
የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዲምትሮ ኩሌባ በገዛ ፈቃዳቸው ከስልጣን መልቀቃቸው ተሰማ፡፡
የሩስያ እና ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ በኋላ በፕሬዝደንት ቮልደሚር ዘለንስኪ አስተዳደር ውስጥ ዋነኛ ሰው ሆነው የሰነበቱት ኩሌባ ምክንያቱን ይፋ ባላደረጉት ምክንያት ከስልጣን ለቀዋል፡፡
ኩሌባ በተለያዩ የአለም ክፍሎች በመዘዋወር የዩክሬን አቋም በማንጸባረቅ ድጋፍ ለማሰባሰብ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴን በማድረግ ይታወቃሉ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ መልቀቂያቸውን ከማስገባታቸው ቀደም ብሎ ከሰሞኑ የዩክሬን ምክትል ጠቅላይ ሚንስትርን ጨምሮ ሶስት የተለያዩ ሚንስትሮች በተመሳሳይ በገዛ ፈቃዳቸው ከስልጣን መልቀቃቸውን የሚያሳውቅ ደብዳቤ አስገብተዋል፡፡
የሀገሪቱ ፓርላማ በነገው እለት በሚያካሂደው ስብሰባ የሚንስትሮቹን መልቀቂያ ተቀብሎ እንደሚወያይ ሲኤንኤን አስነብቧል፡፡
ኩሌባ ከስልጣን የለቀቁት ዘለንስኪ በዚህ ወር ወደ አሜሪካ ለጉብኝት ለማቅናት ዝግጅት እያደረጉ በሚገኙበት ወቅት ነው፡፡
ከዚህ ባለፈም በምስራቃዊ ግንባር ፖክሮቨስክ ከተማን ለመቆጣጠር የሩስያ ጦር እየገፋ በሚገኝበት በዚህ ጊዜ የሚንስትሮቹ ከስልጣን መልቀቅ በዘለንስኪ አስተዳደር ላይ ክፍተት ሊፈጥር እንደሚችል ተነግሯል።
የሚንስትሮችን ከሀላፊነት መነሳት ተከትሎ ንግግር ያደረጉት የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ቮልደሚር ዘለንስኪ መንግስታቸው ትኩስ ሀይል እንደሚያስፈልገው ገልጸዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት አመታዊ ጉባኤ ለመሳተፍ ወደ ዋሽንግተን ከማቅናታቸው በፊት በካቤኔያቸው ያጋጠማቸውን ከፍተት በአፋጣኝ ለመሙላት አዳዲስ ተሿሚዎችን ምልመላ እንደሚጀምሩ ይጠበቃል፡፡
በዚህም ከዘለንስኪ ካቤኔ ውስጥ 50 በመቶዎቹ በአዳዲስ ባለስልጣናት እንደሚተኩ ነው የተነገረው፡፡
ሩስያ በዩክሬን አጠናክራ በቀጠለችው ጥቃት ዩክሬን ከፖላንድ ጋር በምትዋሰንባት የደንበር ከተማ ለቪቭ ከፍተኛ የተባለውን የሚሳኤል ጥቃት መፈጸሟ ተሰምቷል፡፡
በዚህ ጥቃት ሰባት ሰዎች ሲገደሉ 25 ሰዎች ደግሞ ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን በተመሳሳይ በትላንትናው እለት በማዕከላዊ ዩክሬን በወታደራዊ ማሰልጠኛ ተቋም ላይ በደረሰ ጥቃት 53 ሰዎች ሲሞቱ በ270 ሰዎች ላይ ደግሞ ጉዳት መድረሱ ነው የተዘገበው፡፡