የጦር ጀቱ ከሩሲያ የተሰነዘሩ ጥቃቶችን በማምከን ላይ ነበር የተባለ ሲሆን በሩሲያ እንዳልተመታ ተገልጿል።
ዩክሬን ከምዕራባዊያን ያገኘችው ኤፍ-16 የጦር ጀት መከስከሱን ገለጸች።
ዩክሬን ከሩሲያ የሚደርስባትን የአየር ላይ ጥቃቶችን ለማምከን ምዕራባዊያን ሀገራት ኤፍ-16 የተሰኘውን የጦር አውሮፕላን እንዲለግሷት ቆይታለች።
ይህን ተከትሎ ነበር አሜሪካንን ጨምሮ በርካታ የኔቶ አባል ሀገራት ለዩክሬን ኤፍ-16 የተሰኘውን የውጊያ አውሮፕላን ለዩክሬን መስጠት የጀመሩት።
አሜሪካ የለገሰችው የመጀመሪያው ኤፍ-16 የጦር ጀት ባሳለፍነው ሀምሌ ኪቭ ደርሷል።
እስካሁን ዩክሬን ስድስት ኤፍ-16 የጦር ጀት ከወዳጆቿ የተረከበች ሲሆን ከነዚህ መካከል አንዱ ከሰሞኑ ተከስክሷል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
የጦር ጀቱን ሲያበር የነበረው ኦሌክሲ ሜስ የተሰኘው ፓይለት በአደጋው ምክንያት ህይወቱ እንዳለፈ ተገልጿል።
የዩክሬን ጦር ባወጣው መግለጫ ፓይለቱ ዩክሬናዊያንን ከሩሲያ ጥቃት ሲከላከል ህይወቱ እንዳለፈ አስታውቋል።
ተቋሙ አክሎም የጦር አውሮፕላኑ በቴክኒክ ብልሽት አልያም በፓይለቱ ስህተት ምክንያት ሳይከሰከስ እንዳልቀረ፣ የአደጋውን ትክክለኛ ምክንያት ምርመራ እያደረገ መሆኑንም ጠቅሷል።
ዩክሬን ከወዳጅ ሀገራት 130 ኤፍ-16 የጦር ጀቶችን በእርዳታ እንደምታገኝ ተስፋ አድርጋለች።