ሩሲያ የአሜሪካን የተኩስ አቁም ሀሳብ በመርህ ደረጃ እንደምትቀበለው አስታወቀች
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ማንኛውም ተኩስ አቁም ወደ ዘላቂ ሰላም ሊያመራ ይገባል ብለዋል

ወደ ሞስኮ የሚያቀናው የአሜሪካ ልዑክ በዝርዝር ጉዳዮች ላይ ከሩሲያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን አሜሪካ ያቀረበችው የ30 ቀናት የተኩስ አቁም ስምምነት ሀሳብ ማሻሻል የሚገባቸው በርካታ ነጥቦች እንዳሉ ተናገሩ፡፡
ፕሬዝዳንቱ የተኩስ አቁም ሀሳቡን በመርህ ደረጃ መቀበላቸውን ገልጸው ነገር ግን ማንኛውም የተኩስ አቁም ስምምነት ለጦርነቱ መጀመር ምክንያት የሆኑ ዋነኛ አጀንዳዎችን እውቅና እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡
ፑቲን ለአሜሪካ ጥያቄ የሰጡት መልካም ምላሽ ለአሜሪካ ጥረት ያላቸውን ድጋፍ የሚያሳይ እንዲሁም በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ውይይቶች እንዲደረጉበት በር የከፈተ ነው ተብሏል፡
ከዚህ ጎን ለጎን የስምምነት ሰነዱ ባነሳቸው ሀሳቦች ዙሪያ መስተካከል እና መካተት አለባቸው ያሏቸውን ሀሳቦችም በግልጽ አስቀምጠዋል፡፡
ከእንዚህ መካከል ለሩሲያ ደህንነት ዋስትና መስጠት እና የተኩስ አቁም ስምምነቱ ወደ ዘላቂ ጦርነት ማቆም እንዲያመራ የጠየቁባቸው ሀሳቦች ይጠቀሳሉ፡፡
ፑቲን በክሬምሊን ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ "ጦርነቱን ለማቆም በቀረቡት ሀሳቦች ተስማምተናል፤ ነገር ግን ይህ ተኩስ አቁም ዘላቂ ሰላምን የሚያመጣ እና የዚህን ቀውስ ዋና መንስኤዎችን ለማስወገድ የሚያስችል መሆን አለበት ከሚለው እውነታ ጋር እንቀጥላለን” ብለዋል።
በተጨማሪም ሰላም ለማስፈን እየጣሩ የሚገኙትን የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን አመስግነው ሀገራቱ ወደ ሶስተኛው የአለም ጦርነት ተቃርቦ የነበረውን ፍጥጫ ለማርገብ መወሰናቸው በአለም አቀፍ ሰላም ላይ ትልቅ ሚና ያለው ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ትራምፕ በበኩላቸው የፑቲንን ንግግር "በጣም ተስፋ ሰጭ" ሲሉ የገለጹት ሲሆን ሩሲያ ትክክለኛውን ነገር ታደርጋለች የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።
ወደ ሩሲያ የሚያቀናው የአሜሪካ ከፍተኛ ልዑካን ቡድን ከሩሲያ ባለስልጣናት ጋር በሚያደርገው ውይይት ያላለቁ ጉዳዮች እና ዝርዝር ነጥቦች ላይ እንደሚነጋገርም ትራምፕ ገልጸዋል፡፡
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮለድሚር ዘለንስኪ በበኩላቸው “ፕሬዝዳንት ፑቲን የተኩስ አቁም ሀሳቡን ውድቅ ለማድረግ እየተዘጋጁ ነው፤ ነገር ግን ለትራምፕ ለመንገር ፈርተዋል” ሲሉ ክስ የተቀላቀለበት ንግግር አድርገዋል፡፡
ሮይተርስ በዘገባው ሩስያ ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነቶች ዩክሬን ድጋሚ ራሷን ለማደረጃት ልትጠቀምባቸው እንደምትችል ስጋት አላት ፤ በዚህ የተነሳም ዋና ዋና የምትላቸውን ቅድመ ሁኔታዎች በማስቀመጥ የተኩስ አቁሙን የምትቀበልበት እድል ከፍተኛ መሆኑን ዘግቧል፡፡