ፑቲን 'የጥቁር ባህር እህል ስምምነት' በሚታደስበት ጉዳይ ለመነጋገር ዝግጁነታቸውን ገለጹ
ስምምነቱ እንዲደረስ ያደረጉት የቱርኩ ፕሬዝደንት ኤርዶጋን እና ተመድ ሩሲያ ወደ ስምምነቱ እንድትመለስ ፑቲንን ለማሳመን ጥረት እያደረጉ ናቸው
ከስምምነቱ የወጣችው ሩሲያ የራሷን ስንዴ እና ማዳበሪያ ለማስወጣት እንቅፋት እንደገጠማት እና የዩክሬን ስንዴ ችግር ላለባቸው ሀገራት እየደረሰ አይደለም የሚል ቅሬታ ስታሰማ ቆይታለች
የሩሲያ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን 'በጥቁር ባህሩ የእህል ስምምነት' ጉዳይ ለመነጋገር ዝግጁ መሆናቸውን ለቱርኩ ፕሬዝደንት ኤርዶጋን መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ይህ በቱርክ እና በተመድ አማካኝነት የተደረሰው 'የጥቁር ባህር እህል ስምምነት' በጦርነቱ ምክንያት የተስተጓጎለው መንገድ ከስጋት ነጻ ሆኖ ዩክሬን ስንዴ ወደ ውጭ እንድትልክ አስችሏታል።
ነገርግን ባለፈው ሐምሌ ወር ሩሲያ ከስምምነቱ መውጣቷን መግለጿ ይታወሳል።
ሩሲያ ከስምምነቱ የወጣችው የራሷን ስንዴ እና ማዳበሪያ ለማስወጣት እንቅፋት እንደገጠማት እና የዩክሬን ስንዴ ችግር ላለባቸው ሀገራት እየደረሰ አይደለም የሚል ቅሬታ ስታሰማ ቆይታለች።
ስምምነቱ እንዲደረስ ያደረጉት የቱርኩ ፕሬዝደንት ኤርዶጋን እና ተመድ ሩሲያ ወደ ስምምነቱ እንድትመለስ ፑቲንን ለማሳመን ጥረት እያደረጉ ናቸው።
በጥቁር ባህር ዳርቻ በምትገኘው የሩሲያ ሶቺ ከተማ በተዘጋጀው የስብሰባ መክፈታ ላይ በቱርክ ስለሚገነባው የጋዝ ማከማቻ እና የእህል ስምምነቱ ጉዳይ ከኤርዶጋን ጋር እንደሚወያዩ ገልጸዋል።
"የእህል ስምምነቱን ጉዳይ እንደምታነሳው አውቃለሁ።"ሲሉ ፑቲን ለኢርዶጋን ነገረዋቸዋል።
"በዚህ ጉዳይ ለመነጋገር ዝግጁ ነን" ብለዋል ፑቲን።
ሩሲያ ከስምምነቱ ከወጣች በኋላ የዩክሬን እህል ጭነው በጥቁር ባህር በኩል ለማስወጣት በሚሞክሩ መርከቦች ላይ የማስጠንቀቂያ ተኩስ ማሰማቷ ይታወሳል። ከዚህ በተጨማሪም በዩክሬን ወደቦች በሚገኙ የእህል ማከማቻዎች ላይ ጥቃት አድርሳለች።