አሜሪካ የስለላ ድሮኗ በሩሲያ ጄቶች ተመቶ በጥቁር ባህር መከስከሱን ገለጸች
ድርጊቱን “ፍጹም ሃላፊነት የጎደለውና የሙያ መርሃን ያልተከተለ” በሚል የተቃወመች ዋሽንግተን የሩሲያን አምባሳደር ለማብራሪያ ጠርታለች
ሩሲያ በበኩሏ ጄቶቿ ከአሜሪካ ድሮን ጋር አለመላተማቸውን ገልጻ ዋሽንግተን “ጸብ አጫሪ” ድርጊቷን እንድታቆም አሳስባለች
የአሜሪካ ኤም ኪው 9 የስለላ ድሮን በሁለት የሩሲያ ሱ 27 ተዋጊ ጄቶች ጉዞው ተቀልብሶ ጥቁር ባህር ውስጥ እንዲከሰከስ መደረጉን ፔንታጎን አስታውቋል።
አንደኛው የሩሲያ ጄት የድሮኑን ተሽከርካሪ ክፍል (ፕሮፔለር) በመምታቱ የስለላ ድሮኑ ተከስክሶ ወደ ጥቁር ባህር ለመግባት መገደዱንም ነው ዋይትሃውስ የገለጸው።
በጥቁር ባህርና አካባቢው መሰል የስለላ ተግባራትን የምትፈጽመው አሜሪካ በአለምአቀፉ ነጻ የአየር ክልል በሩሲያ ጄቶች ያልተገባ መዋከብ ደርሶብኛል ብላለች።
በአውሮፓ እና አፍሪካ የአሜሪካ የአየር ሃይል አዛዡ ጄነራል ጀምስ ሄከር፥ የሩሲያ ጄቶች ከፊትና ከኋላ ሆነው የአሜሪካን ኤም ኪው 9 ድሮን አለምአቀፍ መርህን ባልተከተለ መልኩ ለ30 ደቂቃ ያህል ማሳደዳቸውን ተቃውመዋል።
አንደኛው የሩሲያ ጄት የስለላ ድሮኗን ተሽከርካሪ ክፍል ወይም ፕሮፔለር በመግጨቱም ድሮኗ ተከስክሳ ወደ ጥቁር ባህር መግባቷን ነው ያብራሩት።
የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከሰተው የአሜሪካ ድሮን መከስከስ ዋይትሃውስን ክፉኛ አስቆጥቷል።
በጉዳዩ ዙሪያ ለኔቶ አባል ሀገራት ማብራሪያ የሰጠችው ዋሽንግተን፥ የሩሲያ አምባሳደርንም ለማብራሪያ ጠርታለች።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር በበኩሉ የሩሲያ ጄቶች ከአሜሪካ ድሮን ጋር ተጋጭተዋል የሚለውን መረጃ ያስተባበለ ሲሆን፥ የስለላ ድሮኗ በሩሲያ ቁጥጥር ስር ባለችው ክሬሚያ አቅራቢያ ስለመታየቷም ነው ያስታወቀው።
በአሜሪካ የሩሲያ አምባሳደር አናቶሊ አንቶኖቭ፥ የአሜሪካ ድሮን የሩሲያን ግዛት ጥሳ ለመግባት መቃረቧ “ጸብ አጫሪ ድርጊት” ነው በሚል ከፔንታጎን የቀረበውን ውንጀላ ተቃውመዋል።
“የአሜሪካ ጦር ወደ ድንበራችን ተጠግቶ የስለላ መረጃ ለመሰብሰብ የሚያደርገው ጥረት ያሳስበናል” ብለዋል።
ሩሲያ እና ዩክሬንን ጨምሮ በርካታ ሀገራትን በሚያዋስነው የጥቁር ባህር የተከሰተውን ጉዳይ ለማጣራት ጊዜ እንደሚወስድ ሬውተርስ ዘግቧል።
ለዩክሬን በቢሊየን የሚቆጠር ወታደራዊ ድጋፍ እያደረገች የምትገኘው አሜሪካ የስለላ መረጃዎችን ለኬቭ እንደምታቀርብ ማመኗን የዘገበው አር ቲ፥ ፔንታጎን የአሜሪካ አውሮፕላኖች ድንበር ጥሰው ሲሰልሉ በሞስኮ የሚወሰድባቸውን እርምጃ “ሙያዊ መርህን ያልተከተለ” በሚል የመግለጽ ልምድ እንዳለው አስታውሷል።