የሩሲያው ፕሬዝዳንት ለሁለት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት ቻይና ገብተዋል
የዩክሬን ጉዳይ እና የኒዩክሌር ሃይል ልማት ፑቲን በቤጂንግ ቆይታቸው ከሚመክሩባቸው አበይት ጉዳዮች መካከል ይገኙበታል
ፕሬዝዳንት ፑቲን ቻይና ያቀረበችውን የዩክሬን የሰላም እቅድ መቀበላቸውን ማሳወቃቸው ይታወሳል
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ለሁለት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት ቻይና ገብተዋል።
ፕሬዝዳንት ፑቲን በቤጂንግ ከቻይናው አቻቸው ሺ ጂንፒንግ ጋር የተገናኙ ሲሆን፥ 75 አመት ያስቆጠረውን የሀገራቱን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ተስማምተዋል።
ፑቲን በዩክሬን “ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ” ከመጀመራቸው ከቀናት አስቀድሞ በቤጂንግ ጉብኝት ሲያደርጉ ሀገራቱ “ገደብ የለሽ” ትብብር መመስረታቸውን ይፋ ማድረጋቸውን ሬውተርስ አስታውሷል።
ፕሬዝዳንቱ ሩሲያን እስከ 2030 ለመምራት ተመርጠው ቃለ መሃላ ከፈጸሙ በኋላ በቻይና የመጀመሪያ የውጭ ሀገር ጉብኝታቸውን ማድረጋቸውም ለትብብሩ የሰጡትን ትኩረት ያሳያል ተብሏል።
ከፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ ጋር ዛሬ በቤጂንግ ሲገናኙም የሀገራቱ ትብብር ጥቅምን ብቻ የሚያሳድድና ሆን ብሎ የሆነ አካልን ለመጉዳት ያለመ አለመሆኑን መናገራቸውን የሩሲያው አርአይኤ ኖቮስቲ የዜና ወኪል ዘግቧል።
የምዕራባውያን ማዕቀብና ጫናን በትብብር እያለፉት መሆኑን የሚገልጹት ቤጂንግ እና ሞስኮ ትብብራቸው በአንድ ሀገር (አሜሪካ) የሚመራ የአለም ስርአት ሊያከትም ይገባል ያላሉ።
ሩሲያ በዩክሬኑ ጦርነት ምክንያት በምዕራባውያን እየደረሰባት ያለውን ጫና ለመቀነስ ቻይና ከፍተኛ ሚና እየተጫወተች መሆኑም ይታመናል።
ቻይና ባትቀበለውም ሩሲያ በዩክሬን እያካሄደችው ለምትገኘው ጦርነት ወታደራዊ ቴክኖሎጂዎችን እያቀረበች ነው የሚሉ ወቀሳ ይነሳባታል።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባለፈው ወር በቻይና ጉብኝት ሲያደርጉ ቤጂንግ ለሞስኮ እያደረገች ያለውን ወታደራዊ ድጋፍ እንድታቆም ማሳሰባቸው አይዘነጋም።
የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ ግን የዋሽንግተንን ማስጠንቀቂያ አይቀበሉትም። የሀገራቱ ትብብር የአለም ስራአትን እንደሚያስተካክል በማመን ከፑቲን ጋር ወዳጅነታቸውን አጠናክረዋል።
በዛሬው እለት ፕሬዝዳንት ፑቲንን ሲቀበሉም ቻይና እና ሩሲያ በአለም ላይ ፍትህ እና እኩልነት እንዲሰፍን በጋራ ይሰራሉ ማለታቸውን ሽንዋ ዘግቧል።
ፑቲን በሁለት ቀናት ጉብኝታቸው በኢነርጂ፣ የኒዩክሌር ሃይልን ለሰላማዊ አገልግሎት ማዋል በሚያስችሉና በንግድና ታዳሽ ሃይል ልማት ዙሪያ በትብብር መስራት የሚያስችሉ ስምምነቶች እንደሚፈረሙ ይጠበቃል።
ሁለት አመት ያለፈውን የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ለማስቆም በቻይና በቀረበው የዩክሬን የሰላም እቅድ ዙሪያም መሪዎቹ እንደሚወያዩ ነው የተገለጽው።
ፕሬዝዳንት ፑቲን በቻይና የቀረበውን የሰላም እቅድ እንደሚቀበሉት መናገራቸው ይታወሳል።
ቻይና እና ሩሲያ ግንኙነት የጀመሩበት 75ኛ አመት በዓል ላይም ይታደማሉ ተብሏል።